Sidama Hawassa
+251-462-12-6495
dagoomuf@sidaamaphi.org

13 ኛዉ የወባ ሳይንሳዊ ምርምር ኔትዎርክ ሲምፖዚየም በሀዋሳ ከተማ እየተካሄደ ነዉ።

በ2030 የወባ በሽታን ለማስወገድ የተቀመጠዉን ግብ ለማሳካት ከፍተኛ ድርሻ ያለዉ ሳይንሳዊ የምርምር ኔትዎርክ ሲምፓዚየም በየዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን በሲምፓዚየሙ ላይ የተለያዩ ጥናትና ምርምር ዉጤቶችና ግኝቶች ቀርበዉ ዉይይት ይደረግበታል።

በሀዋሳ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘዉ 13 ኛዉ የወባ ሳይንሳዊ ምርምር ኔትዎርክ ሲምፖዚየም መክፈቻ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ የወባ በሽታ በገዳይነቱ ብቻ ሳይሆን በመኸር ወቅት ጭምር የአምራቹን የሰዉ ኃይል በማጥቃት በአገራት ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ ነዉ ብለዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዉ አክለዉ እንደገለጹት በኢትዮጵያ በቀለፉት አስርት አመታት ወባን ለመከላከልና በመቆጣጠር በተሰሩ ስራዎች አመርቂ ዉጤቶች መገኘታቸዉን ጠቅሰዉ በ2030 ወባን ከአገራችን ለማስወገድ ስትራቴጂ ተነድፎ ትግበራ ዉስጥ መገባቱን ተናግረዋል።

ከአየር ንብረት ለዉጥና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ በወባ በሽታ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እጅጉን እየጨመረ መሆኑን ያነሱት ዶ/ር ደረጀ ለአብነትም በኢትዮጵያ ባለፉት 9 ወራት 8,563,825 ሚሊዮን ለሚሆኑ የወባ ህሙማን ተጠርጣሪዎች በላቦራቶሪ እና በፈጣን መመርመሪያ ኪት ምርመራ ተደርጎ በወባ በሽታ መያዛቸው ለተረጋገጠላቸው 2,307,860 ሰዎች የህክምና አገልግሎት መሰጠቱን ገልጸዋል። ወባን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ዘርፈብዙ ስራዎች እየተሰሩ ሲሆን በበጀት ዓመቱ 19.7.ሚሊዮን አጎበር ተገዝቶ ለወደ ሀገር ውስጥ የገባ ሲሆን 1,207,897 ሚሊዮን ቤቶችን በፀረ-ወባ ትንኝ ኬሚካል መርጨት መቻሉም ተገልጿል። በተጨማሪም የህብረተሰቡን ንቃተ ህልና ለማሳደግ የተለያዩ የሚድያና ንቅናቄ ስራዎች መሰራቱን ሚኒስትር ዴኤታዉ ገልጸዉ በአንዳንድ አከባቢዎች በጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞችና ጤና ባለሙያዎች የሚሰራዉ የቤት ለቤት ስራ መቀዛቀዝ ስለሚታይ በየደረጃዉ ያለዉ አመራር የህብረተሰቡን ተሳትፎ ባረጋገጠ መልኩ ስራዉ በአግባቡ እንዲሰራ አስፈላጊዉን ክትትልና ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል ብለዋል።

 

ወባን ከአገራችን ለማስወገድ የተያዘዉን ግብ ለማሳካት ጥናትና ምርምር ከፍተኛ ድርሻ ስላለው መንግስት ለዘርፉ ትኩረት መስጠቱን የተናገሩት ዶ/ር ደረጀ በግልም ሆነ በቡድን የሚቀርቡ የጥናትና ምርምር ግኝቶች በግብአትነት ተወሰዶ ከሚመለከተዉ ባለድርሻ አካላት ጋር ተግባራዊ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሠላማዊት መንገሻ በመክፈቻ ንግግራቸው ለሲምፖዚየሙ ተሳታፊዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት አስተላልፈው ክልሉ የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ዘርፈ ብዙ ስራዎችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ብሎም ለማስወገድ የተያዘዉን ግብ ለማሳካት የቁጥጥርና ቅኝት ስራዎች ጎን ለጎን የተለያዩ የጥናት ምርምር ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

የአርማወር ሀንሰን ሪሰርች ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕ/ር አፈወርቅ ካሱ በበኩላቸዉ የወባ በሽታን አስመልክቶ የተሰሩ ጥናትና ምርምር ስራዎች ለዉሳኔ ሰጪ አካልም ሆነ ሌሎች የሚመለከታቸዉ ሁሉ ትልቅ ግብአት መሆኑን ተናግሮ ለአብነትም በምስራቁ  የአገራችን አከባቢ  የተገኘዉ  የወባ አስተላለፊ ትንኝ አዲስ ዝርያ (Anopheles Stephensi) የምርምር ዉጤት መሆኑና በአከባቢ ላይ የወባ እጭ ቁጥጥር ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።  

በስፓዝየሙ ላይ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የምርምር ተቋማት፣ ተመራማሪዎች፣ የአገር ዉስጥና ከዉጪ አገራት የተገኙ የወባ መከላከያ ግብአት አቅራቢ ድርጅቶች ተወካዮች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *