Sidama Hawassa
+251-462-12-6495
dagoomuf@sidaamaphi.org

“በጥናትና ምርምር የታገዘ ሥራ ውጤቱ ከፍተኛ ነው” – ዶክተር ዳመነ ደባልቄ

“በጥናትና ምርምር የታገዘ ሥራ ውጤቱ ከፍተኛ ነው” – ዶክተር ዳመነ ደባልቄ

በደረጀ ጥላሁን

የሳምንቱ እንግዳችን ዶክተር ዳመነ ደባልቄ ይባላሉ፡፡ የሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት ዋና ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ትውልድና እድገታቸው በሲዳማ ክልል ደበባዊ ዞን ሁላ ወረዳ ነው፡፡ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሀገረ ሰላም ከተማ ተምረዋል፡፡ ከ1996 ዓ/ም ጀምሮ በጤና ባለሙያነት፣ በጤና መምህርነት እና ጤና መኮንን ሆነው ሰርተዋል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የትምህርት ደረጃቸውን በማሻሻል ከሀዋሳ ዩኒቨርስቲ በጽንስና ማህጸን ህክምና ዘርፍ ተመርቀዋል፡፡ በአዳሬ አጠቃላይ ሆስፒታል ከአንድ አመት በላይ በጠቅላላ ሐኪምነትም ሠርተዋል፡፡ ከእንግዳችን ጋር ወቅታዊ የጤና ስጋት በሆኑ በሽታዎች እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡

መልካም ንባብ፡-

ንጋት፦ የንጋት እንግዳ ለመሆን ፈቃደኛ በመሆንዎ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ፡፡

ዶክተር ዳመነ፦ እኔም ለተሰጠኝ እድል አመሰግናለሁ፡፡

ንጋት፦ የህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት ዋና ተግባሩ ምንድነው?

ዶክተር ዳመነ፦ በኢንስትቲዩቱ አራት ዋና ዋና ሥራዎች ይከናወናሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል በድንገተኛ፣ በሰው ሰራሽም ሆነ በተፈጥሮ አደጋዎች የሚከሰቱ በሽታዎችን ቅኝት ማድረግና ምላሽ መስጠት አንደኛው ተግባር ነው፡፡ ሁለተኛው ጥናትና ምርምር ማድረግ ነው፡፡ ለምሳሌ ባለፈው አመት ሁለት የጥናትና ምርምር ሥራ የተሰራ ሲሆን ዘንድሮ ደግሞ ሶስት ወሳኝ የተባሉ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ለመስራት ተለይቶ ለክልሉ ቀርቧል። ሌላው የላቦራቶሪ ሥራ ነው፡፡ በክልሉ ደረጃውን የጠበቀ ላቦራቶሪ አለ፡፡ ቀደም ሲል ወደ አዲስ አበባ ተልኮ ይሰራ የነበረው አሁን እዚሁ መስራት ተችሏል፡፡

በቅርቡ ደግሞ በሽታ ሳይነሳ ምልክቱ ካለ ተመርምሮ ምን አይነት በሽታ ነው የሚለውን ለመለየት የሚስችል ዘመናዊ ማሽን እያስመጣን ነው፡፡ ሌላውና አራተኛው ተግባር የመረጃ ቋት ነው፡፡ መረጃዎቻችንን ዘመናዊ በሆነ መንገድ ማደራጀት አስፈላጊ በመሆኑ በትኩረት እየሰራን ነው፡፡ አጠቃላይ በክልሉ ያሉ የጤና መረጃዎች ቋት ውስጥ ይገባሉ፡፡ ይህም ከዚህ በኋላ የምንሰራቸው ሥራዎችን ወረቀት አልባ እንዲሆኑ ያስችላል፡፡

ንጋት፦ በክልሉ የጤና ስጋት የሆኑ በሽታዎች ምንድናቸው?

ዶክተር ዳመነ፦ በክልሉ ሀዋሳ ከተማን ጨምሮ የወባ በሽታ በወረርሽኝ መልክ በተለያዩ ወረዳዎች በስፋት ይታያል፡፡ ከዚህ ሌላ የኩፍኝ ወረርሽኝ በክልሉ 12 ወረዳዎች ተከስቶ ነበር፡፡ አስፈላጊው ህክምና ተደርጎ አሁን ላይ በሁለት ወረዳዎች ላይ የቀረ ሲሆን ከአምስት አመት በታች ለሆኑ ህፃናት ክትባቱ እየተሰጠ ነው፡፡ ስለሆነም የመቀነስ አዝማሚያ አሳይቷል፡፡ ሌላው በአሁኑ ጊዜ በቫይረስ የሚመጣ ጉንፋን መሰል ወረርሽኝ በስፋት ይስተዋላል፡፡ እነዚህ ሶስቱ በክልሉ እንደ ስጋት የሚታዩ ተብለው ተለይተዋል፡፡ ሌላው ከአራት ወር በፊት የኮሌራ በሽታ በክልሉ ተከስቶ የበሽታ ቅኝት በማድረግ አስፈላጊው ህክምና ተሰጥቷል፡፡ አሁን ግን ኮሌራ በክልሉ ምንም እንደሌለ ማወቅ ተችሏል፡፡ ለዚህም የአካባቢና የግል ንጽህና ላይ ግንዛቤ መፈጠሩ አስተዋጽኦ አድርጓል።

ንጋት፦ ወረርሽኞቹ ያስከተሉት ጉዳት እንዴት ይገለፃል?

ዶክተር ዳመነ፦ በክልሉ 250 የሚሆኑ ህፃናት በኩፍኝ ተይዘው ሁለት ህፃናት ናቸው በፅኑ የታመሙት፡፡ የወባ ወረርሽኝ በስፋት ቢታይም ሞት አልተከሰተም፡፡ በቅድሚያ የበሽታ ቅኝትና አሰሳ ስለሚደረግ ህክምና በፍጥነት ማግኘት አስችሏል። በኮሌራ ወረርሽኝ በክልሉ 1 ሺህ 250 ሰዎች ተይዘው ነበረ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 12 ሰዎች ሞተዋል። ወረርሽኙ ከፍተኛ ጉዳት እንዳያደርስ በተደረገው ከፍተኛ ርብርብ እና የግንዛቤ ሥራ አሁን ላይ በክልሉ ምንም የኮሌራ በሽታ የለም፡፡ የወባ ወረርሽኝን በተመለከተ በአጎበር አጠቃቀም ላይ ችግር ነበር፡፡ ይህም በተሰራው የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ችግሩ ተስተካክሏል፡፡ የኬሚካል ርጭትም እየተካሄደ ሲሆን ይህም ከጤና ቢሮ ጋር በመተባበር ተሰርቷል፡፡ አሁን ላይ ወረርሽኙ እየቀነሰ ቢሆንም እንደገና እንዳይከሰት የቁጥጥር ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡ በክልሉ 60 በመቶ የሚሆነው ክፍል ለወባ ተጋላጭ ሲሆን ጉዳት እንዳይደርስ የክትትል ሥራ እየተሰራ ነው፡፡

ንጋት፦ በክልሉ ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች ካሉ ቢገልጹልን?

ዶክተር ዳመነ፦ በክልሉ የቲቢ በሽታ በተለይ ማረሚያ ቤት አካባቢ ይታያል። በሽታው በትንፋሽ ስለሚተላለፍ በስፋት እንዳይሰራጭ እየተሰራ ነው፡፡ በማረሚያ ተቋማት ምልክቶች ሲታዩ ወደ ህክምና እንዲሄዱ በጤና ባለሙያዎች አማካይነት ቅስቀሳ ይደረጋል፡፡ በሽታውን ታራሚዎች ወደ ማረሚያ ሊያመጡት ስለሚችል ከመምጣቸው በፊት ምርመራ የማድረግ ሥራ እየተሰራ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ውስጥ ሆነውም የሚያዙ አሉ፡፡ ስለዚህ ቁጥሩ ከበፊቱ አሁን እየጨመረ ስለሆነ የህክምና ሥራው እየተሰራ ነው፡፡ ሌላው አንዳንድ አካባቢዎች ቁጥሩ ትንሽ ቢሆንም በህፃናት ላይ ከምግብ እጥረት ጋር ተያይዞ የሚታዩ በሽታዎችን ለመከላከል አስፈላጊው ምላሽ እየተሰጠ ነው፡፡

ንጋት፦ በሽታዎችን ለመከላከል የሚሰራው ሥራ እንዴት ይገለፃል?

ዶክተር ዳመነ፦ ተቋማችን በዋናነት በሽታዎች ገና ሳይከሰቱ ቅኝት ያደርጋል። ወረርሽኞች ሊከሰቱ ስለሚችሉ ቅድመ ትንበያ በማድረግ ጤና ቢሮ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲሁም የተለያዩ መገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ህብረተሰቡ እንዲጠነቀቅ ይሰራል፡፡ ጤና ቢሮ በበኩሉ መሰረታዊ የጤና ሥራዎች እንዲጠናከሩ ከእኛ ተቋም ጋር ግንኙነት ያደርጋል፡፡ ወረርሽኝ ከተነሳ በኋላ ደግሞ ጤና ቢሮ ብቻ ሳይሆን ከአደጋ መከላከልና ዝግጁነት፣ ከግብርናና እንዲሁም ከሠላምና ጸጥታ ጋር በቅንጅት እንሰራለን፡፡

ንጋት፦ የቅድመ ዳሰሳ ጥናት ለማካሄድ የሚያስችሉ ሥራዎች በቂ ናቸው?

ዶክተር ዳመነ፦ ዳሰሳ ጥናት ለማድረግ የሚያስችል ደረጃውን የጠበቀ ላባራቶሪ አለ፡፡ በተለይ ኩፍኝ በህፃናት ላይ ምልክት ሲታይ ናሙና ተወስዶ ምርምር ይደርጋል፡፡ በዚህ መሰረት በአንድ ወር ሶስት ህፃናት ላይ የበሽታው ምልክት ከታየ የኩፍኝ ወረርሽኝ ስለሆነ ጤና ቢሮ አስቸኳይ የክትባት አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ሌላው ወረርሽኝ እንዳይከሰት አሰሳ ማድረግ ነው፡፡ በውሃ ወለድ አማካይነት የሚከሰቱ እንደ ኮሌራ የመሳሰሉት በሽታዎች ሊኖሩ ስለሚችሉ ቅድመ ማስጠንቀቂያ እንሰጣለን፡፡ ከዚህ አኳያ ሽንት ቤትና ንጹህ የመጠጥ ውሃ የመሳሰሉ ሽፋኖች አነስተኛ በሆነባቸው አካባቢዎች ለበሽታ ምክንያት ስለሚሆን የጥንቃቄ መልዕክትና ማስጠንቀቂያ ይተላለፋል፡፡ የክትባት ሽፋን ዳሰሳ ጥናትም ይደረጋል። ዝቅተኛ ከሆነ የኩፍኝ ወረርሽኝ ስለሚከሰት የክትባት ሽፋኑን ከ85 በመቶ በላይ ለማድረግ እንሰራለን፡፡ በአጠቃላይ የቅድመ ዳሰሳ ጥናት ሥራዎች በጥሩ ሁኔታ እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡

ንጋት፦ የሚተላለፉና የማይተላለፉ በሽታዎች ሥርጭትን ለመግታት ምን እየተሰራ ነው?

@ Me, [12/28/2023 1:22 PM]
ዶክተር ዳመነ፦ የሚተላለፉና የማይተላለፉ በሽታዎች ተብለው እንደ ሀገር የተለዩ 36 በሽታዎች አሉ፡፡ ስኳር፣ ደም ግፊትና የመሳሰሉት የማይተላለፉ በሽታዎች ቢሆኑም በእኛ ደረጃ የቅኝት ሥራ ይሰራል። በዚህም ህዝቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ የማስገንዘብ ሥራዎች ይሰራሉ፡፡ አስጊ የተባሉትን በመለየት በተቀመጠው ደረጃ ማስጠንቀቂያ እየተሰጠ ክትትል ይደረጋል፡፡ ከተለዩት በሽታዎች በእኛ አካባቢ የማይታወቁ ቢኖሩም በአየር ንብረት ለውጥና በሌሎች ምክንያቶች ሊከሰቱ ስለሚችሉ የቅኝት ሥራ በመስራት አስፈላጊው የመከላከል እርምጃ እንዲወሰድ ይደረጋል፡፡

ንጋት፦ ከሌሎች ተቋማት ጋር በቅንጅት የመስራት ልምዳችሁ እንዴት ይገለፃል?

ዶክተር ዳመነ፦ በሽታን የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራዎችን ከፌደራል መንግስት፣ ከጤና ሚንስቴር፣ ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅተን እንሰራለን። በተለይ ከአጎራባች ክልሎች ጋር ተጋግዘን የምንሰራቸው ስራዎች አሉ። አሁን ላይ ችግሩ ቢቀረፍም በኦሮሚያ ክልል አጎራባች በሆነው በምእራብ አርሲ እንዲሁም ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከጌዴኦ ዞን ጋር ኮሌራ እንዳይዛመት የጋራ ግብረ ሀይል በማቋቋም ሰርተናል፡፡ በምግብ እጥረት ምክንያት የሚከሰቱ በሽታዎችን ለመከላከል ደግሞ ከግብርና እንዲሁም ከአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ጋር በቅንጅት ይሰራል፡፡ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው አጥቢ እናቶች እና ከአምስት አመት በታች ያሉ ህፃናት ላይ የከፋ አደጋ እንዳይደርስ ይሰራል፡፡

በምግብ እጥረት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ወደ ጤና ተቋማት ሄደው ህክምና እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ አገግመው ሲወጡ ደግሞ በአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ድጋፍ ይደረጋል፡፡ ከውሃ ወለድ በሽታዎች ጋር በተገናኘ ደግሞ ከውሃ ቢሮ ጋር ይሰራል፡፡ በዚህ መሰረት ከክልሉ ውሃ ቢሮ ጋር ብዙ ሰርተናል። መልጋ ወረዳ፣ ዳራ፣ ወንዶ ገነት እንዲሁም ይርጋለም ማረሚያ ተቋም ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የንጹህ መጠጥ ውሃ ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡

ንጋት፦ ለሥራችሁ እንደ ችግር የሚነሳው ምንድነው? እንዴትስ ቀረፋችሁት?

ዶክተር ዳመነ፦ በክልሉ የኮሌራ ወረርሽኝ ሲከሰት የግብአት እጥረት ነበር። በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ሳይሆን ከውጪ የሚመጡ በኮሌራ የታመሙ ሰዎች ተኝተው የሚታከሙበት አልጋ እና ድንኳን የመሳሰሉ ቁሳቁሶች እጥረት ነበረብን። ከውጪ የሚመጡ ቁሳቁሶች በዩኒሴፍ በኩል ተገዝተው የሚቀርቡ በመሆናቸው የመዘግየት ችግር ታይቷል፡፡ በሌላ በኩል በሀገር ውስጥ የሚመረቱ መድሀኒትና ሌሎች ቁሳቁሶች በክልሉ መንግስት ድጎማ ተደርጎበት በአስቸኳይ እንዲደርሱ ተደርጓል፡፡ ይህም ጥሩ ሥራ እንድንሰራ አስችሎናል፡፡ በወረርሽኝ ጊዜ ለሚያጋጥሙ የቁሳቁስ እጥረት በሀገር ውስጥ ለመስራት ከቴክኒክና ሙያ ተቋም ጋር በመቀናጀት አልጋ ለማሰራት ታቅዷል፡፡ ከዚህ በኋላ የውጪ ምንዛሪ ወቶባቸው የሚመጡትን እዚሁ በአካባቢ ቁሳቁስ ለመስራት ታስቧል፡፡

ንጋት፦ ቀረ የሚሉት ሀሳብ ካለዎት?

ዶክተር ዳመነ፦ ተቋሙ በሀገሪቱ ካሉ ተመሳሳይ ተቋማት ተወዳዳሪና ምርጥ እንዲሆን እየሰራን እንገኛለን፡፡ በወረርሽኝም ይሁን በተለያዩ ምክንያቶች የሚነሱ በሽታዎች ጉዳት ሳያደርሱ በአጭሩ ለመቆጣጠር የሰው ሀይልና ቁሳቁሶችን እያደራጀን ነው፡፡ ከዚህ ሌላ ላቦራቶሪው ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን እንዲሁም የጥናትና ምርምር ሥራውን በሰው ሀይል አጠናክረን ሰፊ ሥራ ለመስራት እየተንቀሳቀስን ሲሆን በጥናትና ምርምር የታገዘ ሥራ ውጤቱ ከፍተኛ ስለሆነ ትኩረት ሰጥተን እንሰራለን፡፡

ንጋት፦ ለሰጡን ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ስም በድጋሚ አመሰግናለሁ፡፡

ዶክተር ዳመነ፦ እኔም አመሰግናለሁ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *