Sidama Hawassa
+251-462-12-6495
dagoomuf@sidaamaphi.org

የጤና መረጃ መኖር ቁልፉ ሚና እንዳለው ተገለጸ፡፡

በጤናው ዘርፍ ለውጤታማ ውሳኔ ሰጪነት ትክክለኛ የጤና መረጃ መኖር ቁልፉን ሚና እንደሚጫወት ተገለጸ፡፡ ዶክተር ሊያ ታደሰ የጤና ሚኒስትር የመሠረታዊ የበሽታ ጫና አሰራሮች ስልጠና መዝጊያ ሥነ-ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር ትክክለኛ የጤና መረጃ መኖር በጤናው ዘርፍ ለሚኖረው ውጤታማ ውሳኔ ሰጪነት የሚጫወት ሚና እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡

ዶክተር ሊያ አያይዘውም የበሽታዋችን ጫና ለመቀነስ መረጃዎችን በመጠቀም ውጤታማ የጤና ውሳኔዎችን ለመስጠት እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩትና እና በአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል መካከል ያለው አጋርነትን አድንቀው በቀጣይ ሁለቱ ተቋማት ይበልጥ በተቀናጀ መልኩ መስራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡ በመጨረሻም ሚኒስትሯ ለስልጠናው መሳካት አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋናን አቅርበዋል ፡፡

ለአምስት ቀናት ሲከናወን የቆየው እና ከአስራ አራት የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ የጤና ባለሙያዎች ያሳተፈው ስልጠና ዓለም አቀፍ የበሽታ ጫና መረጃዎችን በመጠቀም ውጤታማ የጤና ውሳኔዎችን ለመስጠት የሚያስችል ክህሎትን እና ግንዛቤን ያስጨበጠ እንደነበረ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ በጤና መረጃ አያያዝ፣ ቅመራና ትንተና ስራ ላይ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ብሄራዊ የጤና መረጃ አስተዳደር ቅመራና ትንተና ማዕከል ስራዎች እና ተሞክሮዎችን በዶ/ር አወቀ ምስጋናው ቀርበው በጥሩ አርአያነት በስብሰባው ተካፋዮች ተወስዷል፡፡

በስልጠናው ላይ ከኬንያ፣ ዩጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ጅቡቲ፣ ኢትዮጵያ፣ ማዳጋስካር፣ ኮሞሮስ፣ ሶማሊ፣ ሲሸልስ፣ ታንዛኒያ፣ ኤርትራ እና ሞርሺየስ የተወከሉ ባለሙያዎች ስልጠናውን ተካፍለዋል፡፡ በስልጠናው መዝጊያ ሥነ-ሥርዓት ላይ ዶክተር ሊያ ታደሰ የጤና ሚኒስትር እና ዶክተር ራጂ ታጁዲን በአፍሪካ በሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶች እና የምርምር ዳይሬክተር ለሠልጣኞቹ የምስክር ወረቀት ሰጥተዋል፡፡ ይህ ስልጠና በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት የብሔራዊ የጤና መረጃ አስተዳደር ቅመራና ትንተና ማዕከል፤ በአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ በሽታዎች መቆጣጠሪያ ማዕከል (Africa CDC) እና ከጤና ልኬት እና ምዘና ተቋም (IHME) ጋር በመተባበር የተዘጋጀ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *