Sidama Hawassa
+251-462-12-6495
dagoomuf@sidaamaphi.org

የኮሌራ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ሕብረተሰቡ የመከላከያ መንገዶችን በተገቢው መንገድ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባው ተገለጸ

————————-

ባለፉት አምስት አመታት በአፍሪካ ቀንድ አገራት ከኮቪድ ወረርሽኝ ባሻገር ወቅታዊ በሆኑ ተፈጥሮአዊ እና ሰዉ ሰራሽ አደጋዎች ተፅዕኖ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል፡፡ ከእነዚህም ዉስጥ ከድርቅ ጋር ተያይዞ የሚመጡ አጣዳፊ የስነ-ምግብ እጥረት፣ ኮሌራ እና ሌሎችም ተላላፊ በሽታዎች ወረርሽኝ ዋና ዋናዎቹ ናቸዉ፡፡ ስለሆነም የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከጤና ሚኒስቴር፣ ከክልል ጤና ቢሮዎች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር አደጋዎቹ እንዳይከሰቱ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እየተሰሩ ሲሆን ሲከሰቱም የተጠናከረ የቅኝት ስርአትና የምላሽ ስራዎችን ኢንስቲትዩቱ እያስተባበረ ይገኛል፡፡
በመሆኑም የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በተለያዩ ምክንያቶች በሚደረግ መሰባሰብ የኮሌራ በሽታ ስርጭት እንዳያስከትል ሕብረተሰቡ የበሽታዉን ምንነት በሚገባ በመረዳትና የበሽታውን የመከላከያ መንገዶች ሳይዘናጉ ተግባራዊ በማድረግ ራስንና ሕብረተሰቡን ከኮሌራ በሽታ መከላከል እንደሚገባ እያሳወቀ የሚከተሉትን ምክረ-ሃሳቦችንም እንዲተገብሩ በአጽንዖት ያሳስባል፡፡
. ኮሌራ ከሰዉነት ዉስጥ ፈሳሽንና ጠቃሚ ንጥረ ነገሮችን በብዛት እና በአጣዳፊ ሁኔታ ተደጋጋሚ ተቅማጥና ትውከት በማስከተል ሰዉነትን አዳክሞ የሚገል በሽታ መሆኑን መረዳት
. በሽታው በተበከለ ምግብና ውሃ አማካኝነት ማለትም ንጹህ ባልሆኑ እጆች ምግብን በማዘጋጀት፣ በማቅረብና በመመገብ፤ በበሽታ አምጪ ተህዋስያን የተበከለ የምንጭ፣ የጉድጓድ፣ የወንዝ፣ የዝናብ፣ የቧንቧና ወዘተ ውሃን በመጠቀም፤ ክዳን የሌላቸውና ለዝንቦች የተጋለጡ የምግብ ማስቀመጫና መመገቢያ እቃዎችን በመጠቀም፤ በበሽታ አምጪ ተህዋስያን የተበከሉ ምግቦችን፣ አትክልቶችንና ፍራፍሬዎችን በመመገብ ወዘተ ከሰው ወደ ሰው በከፍተኛ ፍጥነት እንደሚተላለፍ መረዳት፤
. ሁልጊዜ ውሃን አፍልቶ እና አቀዝቅዞ መጠጣት ወይም በውሃ ማከሚያ ኬሚካል የታከመ ውሃ መጠቀም፤
. ምግብን በሚገባ አብስሎ በትኩስነቱ መመገብ፤
. የምግብ እቃዎችን በንጹህ ወይም በኬሚካል በታከመ ውሃ ማጠብ እና መጠቀም፣
. መጸዳጃ ቤትን በአግባቡ መጠቀም እና ንጽህናውን መጠበቅ
. እጅን ከመጸዳጃ ቤት መልስ ፣ ምግብ ከማዘጋጀት ከማቅረብ እና ከመመገብ በፊት፣ ሕጻናትን ካጸዳዱ በኃላ እና ሕጻናትን ጡት ከማጥባት በፊት፣ በበሽታው ለተያዙ ሰዎች እንክብካቤ ካደረጉ በኃላ በንጹህ ውሃና በሳሙና በሚገባ መታጠብ፣
. በኮሌራ በሽታ የታመመውን ሰው ልብስ በፈላ ውሃ መቀቀል ወይም በበረኪናና በልብስ ማጽጃ ሳሙና ዘፍዝፎ ማጠብ፣
. አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት የሚያሳዩ ሰዎችን በአቅራቢያ ለሚገኝ ጤና ተቋም ሪፖርት ማድረግ
. የግልና የአካባቢን ንጽህና በመጠበቅ ዝንቦች እንዳይራቡ ማድረግ
. ፈሳሽና ደረቅ ቆሻሻን በአግባቡ ማስወገድ
. ከታመመ ሰው የሚወጣውን ዓይነ-ምድርና ትውከት ጤነኛውን ሰው እንዳይበክል በጥንቃቄ ማስወገድ
. የሐይማኖት አባቶችና አስተባባሪዎች የሚያስተላፉትን የጤና መልዕክቶች በአግባቡ መተግበር
. የሀይማኖት አባቶች ወይም የፀበል ቦታ አስተባባሪዎች ለፀሎትና ለፀበል ለሚሰባሰቡ ምዕመናን የመፀዳጃ ቤት፣የእጅ መታጠቢያ እና ንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ማመቻቸት
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት
ነሐሴ 1/2016 ዓ.ም

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *