Sidama Hawassa
+251-462-12-6495
dagoomuf@sidaamaphi.org

“እለቱ ሁሉን አቀፍ የጤና ሽፋንን ማሳደግ የሚያስችሉ ስራዎችን በማከናወን ይከበራል”

ዶ/ር መቅደስ ዳባ፣ የጤና ሚኒስትር

______________

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ሁሉን አቀፍ የጤና ሽፋን እና የወባ በሽታ ስርጭትን በማስመልከት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫውም ታህሳስ 3/2017 ዓ.ም በአለም አቀፍ ደረጃ “የመንግስት ኃላፊነት ለጤና” በሚል መሪ ቃል የሚከበረው ሁሉ አቀፍ የጤና አገልግሎት ቀን ሲከበር ሁሉም ህብረተሰብ መሰረታዊ የጤና አገልግሎቶችን ያለ እንግልት ማግኘት እንዲችሉ እየተሰሩ የሚገኙ የጤናው ዘርፍ የሪፎርም ማሻሻያ ስራዎች የሚገመገምበትና ከአጋርና ባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት በቀጣይ የሚተገበሩ የጤናው ዘርፍ አንኳር እቅዶች ትግበራ ላይ አቅጣጫ የሚሰጥበት ይሆናል ብለዋል ዶ/ር መቅደስ፡፡

ሚኒስትሯ አያይዘውም መንግስት ለሴክተሩ የሚሰጠው ትኩረትና የፋይናንስ ምደባ ከአመት አመት እየጨመረ መምጣቱን በመጠቆም በዚህም ዋና ዋና በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተደረጉ ጥረቶች ውጤታማ መሆናቸውን ጠቁመው ሁሉን አቀፍ የጤና ሽፋን የሚለውን አለም አቀፍ መርህ በአገራችን እውን ሆኖ በተጨባጭ አመርቂ ሆኖ እንድናይ ሁሉም ባለድርሻ አካላትና ማህበረሰቡ በቁርጠኝነት መረባረብ አለበት ብለዋል።

አክለውም የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህንን ከማስፋፋት አንጻርም ከ11 ሚሊዮን በላይ አባወራና እማወራ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት አስመልክተው በሰጡት መግለጫም በወባ ዙሪያ ቋሚ ሳምንታዊ የግምገማ መድረክና የሪፖርት ስርዓት በማበጀት የከፍተኛ አመራር የቅርብ ክትትል የሚደረግበት መሆኑን በመግለፅ ጤና ሚኒስቴር ከተጠሪ ተቋማትና ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር በሁሉም ክልሎች የወባ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ተግባራትን ድጋፍና ክትትል የሚያደርጉ ባለሙያዎችን በመሰማራት የተቀናጀ ድጋፋዊ ግምገማና አስፈላጊ የሆኑ የወባ መከላከል ስራዎችን ከአጋር ድርጅቶችና ከክልሎች ጋር በመተባበር ምላሾችን የመስጠት ስራ በማከናወን ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ለበሽታው ስርጭት አመቺ የሆኑ ሁኔታዎች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ያስፈልጋል ያሉት ዶ/ር መቅደስ በዚህም የወባ ትንኝ መራቢያ የሆነ ያቆሩ ውሃን የማፍሰስና የማዳፈን ስራ ፣ የአልጋ አጎበር ስርጭትንና አጠቃቀምን በስፋት ማከናወንና ማሻሻል ፣የቤት ለቤት የኬሚካል ርጭትን ማጠናከር፣ ህብረተሰቡ ስለበሽታው ያለውን ግንዛቤ በጤና ትምህርት እንዲታገዝ ማድረግ፣የሚዲያ ባለሙያዎችም ለማህበረሰቡ ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ በመስጠት የበኩላቸውን ሀላፊነት እንዲወጡ መስራት ላይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።

የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሁሉም ማህበረሰብ ተግባር ስለሚያስፈልግ የሚመለከተው ባለድርሻ አካላት ሁሉ የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ዶ/ር መቅደስ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት በሁሉም ክልሎች ባለሙያዎችን በማሰማራት የሱፐር ቪዠን እና የድጋፍና ክትትል ተግባራትን በማጠናከር የልየታ ስራዎችን በመስራት ለበርካታ ሰዎች ነፃ ምርመራ መደረጉንና የወባ ትንኝ መራቢያ ቦታዎችን ማዳፈንና የቤት ለቤት የኬሚካል ርጭት ስራዎችን በስፋት መከናወኑን የገለፁት ደግም የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ሀይሉ ናቸው፡፡

Website: moh.gov.et

Facebook: Ministry of Health,Ethiopia

Twitter: x.com/fmohealth

YouTube: @FMoHealthEthiopia

Tiktok: moh ethiopia

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *