Sidama Hawassa
+251-462-12-6495
dagoomuf@sidaamaphi.org

በሲዳማ ብ/ክልላዊ መንግስት ሕብረተሰብ ጤና ኢንስትቲትዩት አዘጋጅነት በውቢቷ ሀዋሳ ከተማ በዛሬው ዕለት 10ኛዉ ሀገር አቀፍ የሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎች ቅኝትና ምላሽ (PHEM Forum) ፎረም ተጀመረ

ጥር 30/2017 ዓ.ም ፤ ሲዳማ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት

በሀገር ደረጃ በየአመቱ የሚካሄደው የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎች ቅኝትና ምላሽ ፎረም ሲካሄድ የቆየ ሲሆን 10ኛው ደግሞ በሲዳማ ክልል አዘጋጅነት እየተካሄደ ይገኛል።

ፎረሙን በንግግር የከፈቱት የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር አየለ ተሾመ በንግግራቸው ፥ ባለፉት ጊዜያት አለማችን ብሎም ሀገራችንን ጤና የሚፈታተኑ በርካታ ተፈጥሮአዊ እና ሰው ሰራሽ ድንገተኛ አደጋዎች ሲፈታተኑን እንደነበር አንስተው እንደሀገር በተሰራው ስራ ችግሮቹን መቋቋም ችለናል ብለዋል። እንደሀገር ለመጣው ውጤትም የድርሻቸውን ለተወጡ ባለሙያዎችና ለየደረጃው አመራርም ሚኒስትር ዴኤታው ምስጋና አቅርበዋል።

ዶ/ር አየለ አክለውም በአሁኑ ጊዜ አለማችን የተለያዩ ወረርሽኞችን እያስተናገደች እንደሚትገኝ ፣ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ የድርቅ ችግሮችን ፤ የምግብ እና ውኃ ብክለት ጋር የሚያያዙ ችግሮች ፣ የጀርሞች (ተውሳኮች ) የፀረ ተዋሲያን መድኃኒቶችን መላመድ እንዲሁም የጤና መረጃ ሳይበር ጥቃት መኖር ፣ ከፀጥታ ችግሮች ጋር ተያይዘው የሚፈጠሩ የጤና ችግሮች ፣ የአዕምሮ ጤና እና ሱስ የሚያስይዙ ዕጾች አጠቃቀም የሚፈጥሩትን ችግሮችን ለመከላከልና ለመቋቋም ጠንካራ የጤና አደጋዎች ቅኝት ስርዓት መኖር ወሳኝ እንደሆነ ጠቁመው ለዚሁ ደግሞ የቴክኖሎጅ አጠቃቀማችን ሊሻሻል እንደሚገባ እና ባለድርሻ አካላትን አቀናጅተው ይገባል ብለዋል። የባለድርሻ አካላትንና ማህበረሰቡንም አቀናጅተው በማንቀሳቀስ ተለዋዋጭ የሆነውን የጤና አደጋ ስጋቶችን መከላከል እንደሚገባ የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው ይህን በማድረግም የማይበገር የህብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ስርዓት ለብሄራዊ ጤና ደህንነት መሪ ቃሉን እውን ሊናደርግ ይገባል የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሣይ ሀይሉ በበኩላቸው ፥ ሀገራችን በየጊዜው ሲከሰቱ የነበሩ ተላላፊ እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል እና ለመቋቋም የሚያስችሉ ሥራዎች በየክልሎቹ እንዴት እየተተገበሩ እንደሚገኙ ለመፈተሽ እና በቀጣይ ትኩረት በሚፈልጉ ጉዳዮች ዙሪያ አቅጣጫ የሚቀመጥበት መድረክ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ዶ/ር መሣይ አያይዘውም የ10ኛው ፎረም መሪ ቃሉ ሲታሰብ ካለፈው ዓመት ወዲህ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ እንደሀገር በተሰራው ስራ በዓለም መድረክ የተሻለ ውጤት እንደሀገር የተመዘገበ ውጤት መኖሩን ገልጸው ፤ በወባ መከላከልና ቁጥጥር አኳያም የበሽታውን ጫና በ50% ለመቀነስ የተጣለውን ግብ በተሻለ ሁኔታ በ52% ማሳካት እንተቻለም በመጠቆም በዚህ ፎረም ትኩረት የሚሹ ተያያዥ ጉዳዮችም ይዳሰሳሉ ብለዋል።

በመድረኩ ላይ ተገኝተው የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሰላማዊት መንገሻ በባስተላለፉት መልዕክት ፥ የጤናው ሴክተር ዋናው ራዕይ ”ጤናማ አምራችና የበለጸገ ህብረተሰብ ማፍራት ” መሆኑን በመጠቆም ይህ እንዲሳካ ህብረተሰቡን
ከተላላፊ እና ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎችና እንዲሁም ከተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ድንገተኛ አደጋዎች መከላከል እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በማያያዝም በክልሉ ህብረተሰቡን ለአደጋ ሊያጋልጡ የሚችሉ ተፈጥሮአዊ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን ለመከላከልና ሊያስከትሉ የሚችሉትን ጉዳት ለመቀነስ የሚያስችሉ ሥራዎችን አጠናክሮ ከመምራት አኳያ ያሉ ጉድለቶችን ለመሙላት ”ለላቀ ውጤት እና ለጥራት እንስራ ኢኒሼቲቪ ” ተቀርጾ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቁመው በተሰራው ስራም የማይበገር የህብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ስርዓት ለመፍጠር የሚያስችል መደላድል እየተፈጠረ እንደሚገኝ ዶ/ር ሰላማዊት ተናግረዋል ።

የፎረሙ አዘጋጅ የሆነው የሲዳማ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ዳመነ ደባልቄ በበኩላቸው :- በክልሉ አዘጋጅነት የሚካሄደው የህብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎች ቅኝትና ምላሽ ፎረም ክልሉ እንዲያዘጋጅ በመደረጉ የተሰማቸውን ደስታ በመግለጽ ፤ 10ኛው ፎረም ”የማይበገር የህብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ስርዓት ለብሄራዊ ጤና ደህንነት ” በሚል መሪ ቃል እንደሚካሄድ ገልጸዋል ።

በመጨረሻም በፎረሙ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር አየለ ተሾመ፣ የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽኔር አምባሳደር ዶ/ር ሽፈራው ተ/ማሪያም ፣ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ እና ሌሎች የፌደራል እንግዶች ፣ የክልሉ ፕሬዝዳንት ማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ አቶ ባጥሶ ዌዲሳ ፣ የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሰላማዊት መንገሻ ፣ የክልሉ ጤና ቢሮው ማኔጅመንት ፣ የክልሎች / ከተማ ጤና ቢሮ እና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል ።

መድረኩ እስከ የካቲት 02/2017 የሚቀጥል ሲሆን የተለያዩ ሪፖርቶች ፣ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች እና ተያያዥ አጀንዳዎች ቀርበው ውይይት እንደሚካሄድባቸው የወጣው መርሃ ግብር ያሳያል።

የሲዳማ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስት ቲዩት
ጥር 30/2017 ዓ.ም
ሐዋሳ

ተጨማሪ መረጃዎችን የሲዳማ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት
ነፃ የስልክ መስመር፡ 7794
Web site: https://www.sphi.gov.et/

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *