
ኢንስቲትዩቱ የዘመቻ ክትባቱን አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር የንቅናቄ መድረክ እያደረገ ይገኛል፡
የሲዳማ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ዳመነ ደባልቄ በመልዕክታቸው ፥ የፖሊዮ በሽታን እንደ ሀገር ለማጥፋት ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ ስራዎች ቢሰሩም አሁንም በሽታው አለመጥፋቱን ገልፀዋል ።
ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም እንደ ሲዳማ ክልል የተከሰተ የፖሊዮ በሽታ ባይኖርም እንደሀገር በሰባት ክልሎችና አዲስ አበባ ከተማ ምልክቶች በመታየታቸውና በአጎራባች አከባቢዎች በመከሰቱ ክልላችንን ጨምሮ በአሥር ክልሎች ክትባት ለመስጠት መታቀዱን ገልጸዋል።
ህጻናትን የሚያጠቃው የፖሊዮ በሽታን ለመከላከል ከዚህ በፊት ቢከተቡም ባይከተቡም አሁን በዘመቻ የሚሰጠውን ክትባት መውሰድ እንዳለባቸው ታሳቢ በማድረግ በዘመቻ እንዲሰጥ መወሰኑንም ተብራርቷል ።
የተቀናጀ የመጀመሪያው ዙር የፖሊዮ ክትባት ዘመቻው ከየካቲት 14_17 ዓ.ም ቤት ለቤት የሚሰጥ ሲሆን በክትባት ዘመቻው ከአምስት አመት በታች የሆኑ ሌሎች ክትባቶችንም በመደበኛው መርሃ-ግብር ተደራሽ ያልሆኑ ወይም ጀምረው ያቋረጡ ህፃናትን በመለየት ፤ በጤና ተቋማት ወይንም በጊዜያዊ የክትባት መስጫ ጣቢያዎች ተደራሽ እንደሚደረግም ተገልጿል።
ከክትባቱ ዘመቻው ጋር በተቀናጀ መልኩ የቆልማማ እግር (Club Foot) ችግር ያለባቸው ሕፃናትን ለመለየትና ህክምና እንዲያገኙ የማድረግ ስራ እንደሚሰራ ተገልጿል።
በመሆኑም ለተቀናጀ ክትባት ዘመቻው ውጤታማነት ወላጆች አሳዳጊዎችና ባለ ድርሻ አካላት ፣ ትምህርት ቤቶች ፣የሃይማኖት አባቶች ፣የሚዲያ አካላት እና መላው የህብረተሰብ ክፍል ለዘመቻው ስኬታማነት አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ዶ/ር ደመነ ደባልቄ ጥሪያቸውን አቅርበዋል ።
ፖሊዮ ወይም በተለምዶ የልጅነት ልምሻ የሚባለው በሽታ በልጆች ላይ ሽባነትን ወይም ሞትን ሊያስከትል የሚችል በሽታ ሲሆን በክትባት ግን መከላከል ይቻላል መልዕክት በቀረበው ሰነድ ተብራርቷል ።
የንቅናቄውን መድረክ የክልሉ ምክር ቤት ማህበራዊ እና የሴቶችና ህጻናት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ክብርት ወ/አየለች ሌዳሞ ፣ የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል የቢሮ ኃላፊና የጤና ፕሮግራሞች ዘርፍ ኃላፊ አቶ በላይነህ በቀለ ፣ የኢኒስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ዳመኔ ደባልቄ በመምራት ዘመቻው የሚመራበትን ጠንከር ያለ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
በዘመቻው አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ዕድሜያቸው ከአምስት አመት በታች የሆኑ ህፃናት እንደሚሸፈኑ በቀረበው ዕቅድ ተመላክቷል።
በመጨረሻም በመድረኩ የክልሉ ምክር ቤት ማህበራዊ እና የሴቶችና ህጻናት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ክብርት ወ/አየለች ሌዳሞ እና ምክትላቸው አቶ ሀንቻሞ ዩንኩራ ፣ የጤና ቢሮ የማኔጅመንት አባላት ፣ሴክተር መስሪያቤቶች ፣ የዞንና የወረዳ የጤና ዘርፍ የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ ።
የሲዳማ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት
የካቲት 10/2017ዓ/ም
ሀዋሳ
ተጨማሪ መረጃዎችን የሲዳማ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት
ነፃ የስልክ መስመር፡ 7794
Web site: https://www.sphi.gov.et/











