Sidama Hawassa
+251-462-12-6495
dagoomuf@sidaamaphi.org

“ባልተጠበቀ መልኩ እየጨመረ ያለውን የወባ ስርጭት ለማጥፋት ከርዕሳነ መስተዳድር እስከ ቀበሌ አመራር ያሉ የስራ ኃላፊዎች ከሚያከናውናቸው የልማት ስራዎች ጎን ለጎን አጀንዳ ሊያደርጉት ይገባል።” የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴዔታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ

የከፍተኛ አመራር እና የባለድርሻ አካላት ወቅታዊ የወባ ስርጭት ጫናን በዘላቂነት የመግታት አድቮኬሲ መድረክ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሚዛን አማን ከተማ ተካሂዷል።
የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴዔታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ባልተጠበቀ ሁኔታ እየጨመረ የመጣውን የወባ በሽታ ስርጭት በህብረተሰቡ ላይ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችን አስከትሏል ብለዋል። በሀገራችን 75 ከመቶ የሚሆነው አካባቢ ለወባ በሽታ ስርጭት አመቺ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትር ዴዔታ፣ የወባ በሽታ ስርጭት ለህብረተሰባችን የጤና ስጋት እየሆነ መምጣቱን የተደረጉ ጥናቶች ስለሚያመለክቱ በተለይ ከፍተኛ አመራሩ አጀንዳ እንዲያደርገው አሳስበዋል።
ዶክተር ደረጀ አክለውም እንደ ሀገር በአማራ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ ምዕራብ እና ኦሮሚያ ክልሎች ስርጭቱ እየተስፋፋ መሆኑን፣ በተለይ በሰሜን ምዕራብና በደቡብ ምዕራብ 222 ወረዳዎች ላይ የወባ በሽታ ስርጭት መጨመሩን ተናግረዋል።
አገራችን በተለያየ ጊዜያት አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተቀናጅተን በመስራት እንዳለፈቻቸው ያስታወሱት ሚኒስትር ዴዔታ ልክ እንደ ኮቪድ 19 በክላስተር ግብረ ኃይል በማዋቀር ለቀጣይ ስድስት ወራት ባለድርሻ አካላትና አጋር ድርጅቶችን በማቀናጀት ስርጭቱን በእጅጉ ለመቀነስ ጤና ሚኒስቴር ጥብቅ ድጋፍ እና ክትትል እንደሚያደርግም ገልፀዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በበኩላቸው ክልሉ የጀመራቸውን የጤና ልማት ስራዎች ማስቀጠል የሚቻለው ማህበረሰቡ ጤናማ ሲሆን እንደሆነ እና አሁን ያለው የወባ ስርጭት ስጋት እንደሆነባቸው አሳውቀዋል።
በወባ ምክንያት እየደረሰ ያለዉን ማህበራዊና እኮኖሚያዊ ቀዉስ ለመግታት ሁሉም በቅንጅት ልሰራ ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድር የመድሀኒት አቅርቦት ኤጀንሲ መቀመጫውን በክልሉ ያደረገ አሰራር እንዲዘረጋ እና የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ በአፋጣኝ ጥራቱን የጠበቀ የአጎበርና ኬሚካል ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ሀይሉ ኢንስቲትዩቱ የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ በርካታ ስራዎችን እያከናወነ እንደሆነና በአለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የአየር ንብረት ለውጥ ለወባ ትንኝ መራባት ምክንያት መሆኑን፣ የፀጥታ ችግር ባለባቸው አንዳንድ አካባቢዎች በታሰበው ልክ ስራዎችን ለመስራት ተግዳሮት እንደሆነም ገልፀዋል።
ዶክተር መሳይ የችግሩን አሳሳቢነት ሁሉም እንዲረዳው አሳስበው፤ የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የበሽታ አስተላላፊ ትንኞች ላይ የዘረ መል ልየታ ቅኝት እንደሚሰራም ተናግረዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም በበኩላቸው የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር 1.2 ሚሊዮን አጎበር መሰራጨቱንና 117 ሺህ 810 ቤቶች የኬሚካል ርጭት መደረጉን ገልፀዋል።
ባለፉት 11 ወራት ውስጥ 959 ሺህ 944 ሰዎች የወባ ምልክት ታይቶባቸው 538 ሺህ 327 ሰዎች ወይም 56% የሚሆኑ የህብረሰብ ክፍሎች የወባ ተዋስያን በደማቸው የተገኘባቸዉ በመሆኑ የበሽታውን ስርጭት አሳሳቢ በማድረጉ የሚመለከታቸው አካላት በጉዳዩ እንዲመክሩበትና መፍትሔ እንዲሰጡም አቶ ኢብራሂም ጠይቀዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ ዶክተር ሰላኢ እና የአለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ፕሮግራም ዶክተር ፒተር የኢትዮጵያ መንግስት ለጤናውዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑ እሚያበረታታ መሆኑን ጠቁመው። የወባን በሽታ ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረጉ ስራዎች ድጋፍ እና ክትትላቸው እንደሚቀጥል አሳውቀዋል።
በምክክር መድረኩ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾን ጨምሮ የኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት የሁሉም ክልሎች የጤና ቢሮ አመራሮች፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የአለም ጤና ድርጅት ተወካዮች፣ አጋር ድርጅቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን ሁሉም አመራር ወባን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት በሚደረገው ዘመቻ ግምባር ቀደም በመሆን እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።
Website: moh.gov.et
Facebook: Ministry of Health,Ethiopia
Twitter: twitter.com/FMoHealth
YouTube: @FMoHealthEthiopia
Tiktok: @mohethiopia

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *