
የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ፤ ሕዳር 22/2017ዓ.ም
በጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ በክብርት ወ/ሮ ፍሬህይወት አበበ የሚመራ የተቀናጀ ድጋፍዊ ክትትል ቡድን ከቢሮው ማኔጅመንት እና ከተጠሪ ተቋማት ኃላፊዎች አባላት ጋር ውይይት አድርገዋል።
የተቀናጀ ድጋፍዊ ክትትል የሚያደርገው የጤና ሚኒስቴር ቡድን በሲዳማ ክልል ሥር የሚገኙ በአራት ዞኖች ፣ ስምንት ወረዳዎች ፣ አራት ሆስፒታሎችን ፣ ስምንት ጤና ጣቢያዎችን እና ስምንት ጤና ኬላዎችን እንዲሁም እስከ ነዋሪው 40 አባወራ/እማወራዎችን (ህብረተሰብ ድረስ ) ያለውን በክልሉ በበጀት አመቱ እስካሁን የተሰሩ ስራዎችን ምልከታ እንደሚያደርጉ ተገልጿል።
የተቀናጀ ድጋፋዊ ክትትል ቡድኑ በመስክ ምልከታው የወባ መከላከልና ቁጥጥር ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ አሃድ የሥራ ሁኔታ፣ ለስራው አስፈላጊ የሆኑ መድኃኒቶችንና የህክምና መገልገያዎች አቅርቦትና አያያዝ እንዲሁም የነዋሪው ህብረተሰብ ስለ ጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም አተገባበርና የነበራቸው ግንዛቤ በምን ደረጃ እንደሚገኝ
ተዘዋውሮ እንደሚመለከቱ ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ ወ/ሮ ፍሬህይወት አበበ ገልጸዋል ።
ሚኒስትር ዴኤታዋ አክለውም ከጤና ሚኒስቴርና ከተጠር ተቋማት በቅንጅት በክልሉ በተመረጡ ጤና ተቋማት የመድኃኒት አስተዳደር ሥርዓቱን በሚመለከት ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ክትትልና ቁጥጥር ሲያደርግ የነበረ ቡድንም በዚሁ መድረክ ገብረ-መልስ እንደሚያቀርብ እና ሌላው በወባ እና የመጀመሪያ ደረጃ የጤና ክብካቤ አሃድ ስራ እንቅስቃሴን የሚደግፍና የሚከታተለው ቡድን ይዞ የሚወርደውንም ቼክ ሊስት እንደሚቀርብ ጠቁመው ፤ በእነዚህ በሁለቱ ቡድኖች የመስክ ምልከታ ሪፖርት እና በአዲስ መልክ ከዛሬ ጀምሮ የሚወርደው ቡድን ቼክ ሊስት ቀርበዋል።
በዚሁ መሠረት ቀደም ስል ክትትል ሲያደርግ የነበረው ቡድን ከመድኃኒት አያያዝ እና አጠቃቀም ላይ የታዩ ጠንካራ ጎኖቹ ይበልጥ እንዲጎለብቱ እና በጉድለት የተለዩ ችግሮችን ስለሚሻሻሉበት ሁኔታ ላይ ጠንከር ያለ ውይይት ተደርጓል።
ከዚህም ባሻገር ከጤና አገልግሎት አሠጣጥ አኳያ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና እንደ አገር እየጨመረ የመጣው የወባ በሽታ በህብረተሰቡ ላይ ሊፈጥር የሚችለውን ጫና ለመከላከልና ለመቆጣጠር ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ሊሰሩ የሚገቡ ስራዎችን በሚመለከት ከዛሬ ጀምሮ ወደ ታች የሚወርደው ቡድንም ድጋፍና ክትትሉን እንደጨረሰ በተገኘው ግብዓት መነሻነት በክቡራን እንግዶቹ የቀጣይ አቅጣጫዎች ይቀመጣሉ ብለዋል ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ ወ/ሮ ፍሬህይወት ።
የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሰላማዊት መንገሻ በበኩላቸው ቡድኑን እንኳን ደህና መጣችሁ የሚል መልዕክት ባስተላለፉበት ንግግራቸው የጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች እና ከፍተኛ ባለሙያዎች በክልላችን በየጊዜው እየተገኙ የሚያደርጉልን ድጋፍና ክትትል የሚደነቅና እንደክልል ውጤታማ የሆነ ስራ እንዲሰራ በእጅጉ የሚያግዝ ነው ብለዋል ። አያይዘውም በመጀመሪያው በመድኃኒትና ህክምና መገልገያዎች አስተዳደር ላይ በቡድኑ የተለዩ ቁልፍ መሻሻል የሚገባቸው ችግሮች ላይ የተሻለ ስራ ተሠርቶ እንዲሻሻሉ ይደረጋልም ብለዋል። ይህን ለማድረግ እንደክልል የተቀረጸው ”ለላቀ ውጤትና ጥራት እንስራ” ኢንሼቲቪ እንዳለ ጠቁመው የየደረጃው የዚሁ ኢንሼቲቪ ተዋናዮች አጀንዳ እንዲሆን በማድረግ ችግሮቹን መቅረፍ እንደሚቻልም የቢሮ ኃላፊዋ ዶ/ር ሰላማዊት ገልጸዋል።
የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ
ሕዳር 23/2017 ዓ.ም




