Sidama Hawassa
+251-462-12-6495
dagoomuf@sidaamaphi.org

ለፅዱ ጎዳና ኑሮ በጤና” ጥሪ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ይገባል – ዶ/ር መቅደስ ዳባ

ንፅህና ለህብረተሰብ ጤና ስርዓት ያለው ሚና የጎላ በመሆኑ “ለፅዱ ጎዳና ኑሮ በጤና” ጥሪ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ይገባል ሲሉ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ገለፁ፡፡

“ጠንካራ የህብረተሰብ ጤና አደጋ ምላሽ ለማይበገር የጤና ስርዓት ግንባታ” በሚል መሪ ቃል የህብረተሰብ ጤና አደጋ ምላሽ ማሻሻያ ላይ ያተኮረ የንቅናቄ መድረክ በጅግጅጋ ከተማ ተጀምሯል።

በመድረኩ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሁመድ የህብረተሰብ ጤና አደጋ ምላሽ አሰጣጥ ይበልጥ ስኬታማ እንዲሆን የፋይናንስ ስርዓትን ማሳደግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ይህም ድንገተኛ ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ ምላሽ ለመስጠት የሚያስፈልገውን በጀት ለማፈላለግ የሚወስደውን ጊዜ በመቀነስ በሰው ህይወት እና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ያግዛል ብለዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው፤ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች በሰው ህይወት እና በኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተሉ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ባለፉት 5 ዓመታት ለጤና ዘርፉ ልዩ ትኩረት ተሰቶ እየተሰራ እንደሚገኝ ያነሱት ሚኒስትሯ፤ በተለያዩ ወቅቶች ለተከሰቱ ወረርሽኞች በቂ ምላሽ ለመስጠት በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልፀዋል።

ንፅህና ለጠንካራ የህብረተሰብ ጤና ስርዓት ያለው ሚና የጎላ በመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላቀረቡት “ለፅዱ ጎዳና ኑሮ በጤና” ጥሪ ምላሽ በመስጠት የህብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ስርዓትን ይበልጥ ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

እስካሁን ለተከሰቱ የኮሌራ፣ ደንጊ ትኩሳት፣ አጣዳፊ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እና የኩፍኝ ወረርሽኝ በቂ ምላሽ መሰጠቱን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መሳይ ሀይሉ በመድረኩ ተናግረዋል።

ከ19.6 ሚሊዮን በላይ የአልጋ አጎበር ስርጭት መደረጉን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የኩፍኝ ወረርሽኝ ከተከሰተባቸው 4 መቶ ወረዳዎች በ320 ወረዳዎች ላይ በቂ ምላሽ በመስጠት መቆጣጠር ተችሏል ብለዋል።

በቀሪዎቹ የተጠናከረ የአደጋ ምላሽ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ያነሱት ዋና ፋይሬክተሩ በጤና ሚኒስትር እና በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት የተጀመረው ንቅናቄ ቅንጅታዊ አሰራርን በማዳበር የህብረተሰብ ጤና አደጋ ምላሽ ስርዓትን ውጤታማ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎችም “ለፅዱ ጎዳና ኑሮ በጤና” ጥሪ ምላሽ የበኩላቸውን ድጋፍ አድርገዋል።

በቴድሮስ ታደሰ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *