የAVoHC-SURGE ስልጠና ተሳታፊዎች በሲዳማ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጉብኝት ማድረጋቸው ተገለጸ።

የሲዳማ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት

ሰኔ 19/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከአለም አቀፍ አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ከሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች የተወጣጡ የ4ኛ ዙር የአፍሪካ በጎ ፈቃደኞች የጤና ኮርፕስ (AVoHC-SURGE) ስልጠና ተሳታፊዎች በሲዳማ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የስራ ጉብኝት አደረጉ።

የጉብኝቱ ዋና ዓላማ በኢንስቲትዩቱ የህብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎችና የወረርሽኞች ምላሽ መስጫና ማስተባበሪያ ማዕከል (PHEOC) እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን በመጎብኘት የተግባር ልምድ መቅሰምና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ታላሚ ያደረገ መሆኑ ተገልጿል።

ሠልጣኞቹን በመቀበል የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የሲዳማ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎች ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በድሉ ባዴጎ እንደገለጹት፥ ጉብኝቱ ለአንድ ወር በሚቆየው የAVoHC-SURG ስልጠና ውስጥ ከተካተቱት የተግባር ልምምዶች (Practical Session) መካከል አንዱ መሆኑን ገልጸዋል ።

አቶ በድሉ አክለውም የPHEOC ማዕከሉ ወረርሽኞችንና ሌሎች የህብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎች ሲከሰቱ ፈጣን ምላሽ በመስጠት እያከናወነ ያለውን አበይት ተግባራት ለሰልጣኞቹ በዝርዝር ገለፃ አድርገዋል።

በጉብኝቱ ወቅት የኢንስቲትዩቱ PHEOC ማናጀር አቶ በላይ አለማየሁ ስለ ማዕከሉ አጠቃላይ አደረጃጀት፣ የስራ ሂደት፣ የተገኙ ውጤቶች እና እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት ላይ ገለጻ አቅርበዋል።

ከ100 በላይ የ4ኛው ዙር AVoHC-SURGE ሠልጣኞች በጉብኝቱ የተሳተፉ ሲሆን፣ ተሳታፊዎቹ በሰጡት አስተያየት በማዕከሉ የጎበኙትና ያገኙት ተግባራዊ ልምድ ለሙያዊ አቅማቸው ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ገልጸው፣ ጉብኝቱ የንድፈ-ሀሳብ ስልጠናውን ከተግባር ጋር ለማዛመድ እጅግ በጣም አስፈላጊ መሆኑን አስታውቀዋል።

ለአንድ ወር የሚቆየው ይህ ስልጠና የህብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎችን የመከላከል፣ የመለየትና ፈጣን ምላሽ የመስጠት አቅምን በአፍሪካ አገራት ለማጠናከር እንደሚያግዝ ይጠበቃል።

የሲዳማ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት

ሰኔ 19/2018 ዓ/ም

ሀዋሳ

ለተጨማሪ የመረጃ አማራጮች

👇👇👇👇 ይመልከቱ

ነፃ የስልክ መስመር፡ 7794

Web site: sphi.gov.et/emergency

Facebook: https://web.facebook.com/profile.php?id=100083576610173

Telegram: https://t.me/c/1865772308/1

Email:- admin@sphi.gov.et

See less

Similar Posts

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *