በመድረኩ የሲዳማ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምትክል ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡጋሞ ሀናጋ እንደተናገሩት ኢንስቲትዩቱ ከተቋቋመበት ዓላማዎች መካከል አንዱ በምርምር ላይ የተመሰረተ የጤና መረጃ በማመንጨት ውሳኔ ሰጪ አካላት እንዲጠቀሙበት ማድረግ እና የምግብና ስርዓተ – ምግብ ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ እና በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ማስተባበር መሆኑን ገልፀው በሚጠበቀው ልክ እየተሰራ ባለመሆኑ በክልሉ ከጉዳዩ ጋር የተያያዙ ዘርፈ ብዙ ችግርን በሚገባ የጋራ ግንዛቤ በመያዝ በአንድነትና በትብብር ተግባራትን ለይቶ መስራት ይገባል ብለዋል።
የፕሮጀክቱ መኖር ለክልሉ ማህበረሰብ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን የተናገሩት ምትክል ዋና ዳይሬክተሩ የምግብና ስርዓተ – ምግብ ፖሊሲን ወደ ተግባር መለወጥና መረጃ ላይ ተመስርቶ ምን ያህል ህፃናት የስርዓተ-ምግብ ተጠቃሚ መሆናቸውንና ተደራሽ ያልሆኑትን ለይቶ በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ምላሽ እንዲያገኙ ይሰራል ብለዋል።
አክለውም እንደ ሲዳማ ብዙ የሚጠበቁብን ስራዎች አሉ ያሉት ምትክል ዋና ዳይሬክተሩ በዕለቱ የተገኙ ተሳታፊዎች በጉዳዩ ብዙ ልምድ እና እውቀት ያለቸው በመሆኑ በቋሚነት መገናኘትና መምከር እንዲሁም ተግባራትን መገምገም፤ ሃብት በጋራ ማፈላለግና መጠቀም፤ የግንዛቤ ፈጠራ ስራዎችን በሴክተር ተቋማት በቅንጅት መስራት እንደሚጠበቅ አሳስበዋል።
በመድረኩ የኢንስቲትዩት ጥናትና ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር እና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ተመስገን ታደለ ፕሮጀክቱ ያለበትን ሁኔታ እንዲሁም ስርዓተ-ምግብ የሚሹ ጉዳዮችን በተመለከተ ሰነድ አቅርበዋል።
በክልላችን ያሉትን የምግብና ስርዓተ ምግብ ችግሮችን ለመፍታት ትክክለኛ መረጃ መስጠት እንደሚጠበቅ የጠቆሙት አቶ ተመስገን የፕሮጀክቱ ቀጣይነት ላይ መስራት እንደሚገባ ገልፀዋል።
በመድረኩ የሚመለከታቸው የሴክተር መስሪያ ቤቶች እና የአጋር አካላት ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
የሲዳማ ሕብረተስብ ጤና ኢንስቲትዩት
ጥቅምት 18/2017 ዓ.ም
ሀዋሳ