የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ዋና ከተማ፣ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ እና የአህጉራዊ አንድነት ተምሳሌት የሆነችው አዲስ አበባ፣ በጤናው ዘርፍ አህጉራዊ ታሪክ ያተረፈ ታላቅ ጉባኤ ከሰሞኑ አስተናግዳለች። ከመላው አፍሪካ (ከምዕራብ፣ ከምስራቅ፣ ከማዕከላዊ እና ከደቡብ) ከተውጣጡ 36 ሀገራት የመጡ የጤና ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች፣ የህዝብ ጤና ተቋማት መሪዎች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ አካዳሚክ ተቋማት እንዲሁም አለም አቀፍ አጋሮች በጉባኤው ላይ ተሳትፈዋል፡፡
ይህ ታሪካዊ መድረክ “ካውንትዳውን 2030” (Countdown 2030) በመባል የሚታወቅ ሲሆን፣ አህጉሪቱ ወደ 2030 የዘላቂ ልማት ግቦች (SDGs) የምታደርገውን ጉዞ ፍጥነትና ውጤታማነት በጋራ ለመገምገም የተዘጋጀ ነው። ቀደም ሲል በሚሊኒየም የልማት ግቦች (MDGs) ዘመን ተጀምሮ የነበረው ይህ ንቅናቄ፣ አሁን ላይ የአፍሪካ ሀገራት በጤናው ዘርፍ ያመጧቸውን ለውጦች፣ በተለይም የእናቶች፣ የጨቅላ ህፃናት እና የህፃናት ጤና አጠባበቅ ላይ የተመዘገቡ ስኬቶችንና የሚቀሩ የቤት ስራዎችን በሳይንሳዊ መረጃ አስደግፎ ለመገምገም አስችሏል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ በጉባኤው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ኢትዮጵያ ይህንን አህጉር አቀፍ የቴክኒክ ባለሙያዎችና መሪዎች ጉባኤ ስታስተናግድ የመጀመሪያዋ መሆኑን ጠቅሰው፣ መድረኩ ለሀገሪቱ ትልቅ እውቅና እና ምርታ መሆኑን ገልጸዋል።“ይህ ጉባኤ ሀገራት በጋራ ትምህርት የሚወስዱበት፣ ከአንዱ ሀገር ወደ ሌላው ልምድ የሚቀስሙበት ወሳኝ መድረክ ነው፤ በተለይም በትምህርት ተቋማት፣ በመረጃ ተቋማት እንዲሁም በመንግስት አካላት መካከል ያለውን የመረጃ ፍሰት በማየት ‘መረጃዎች ምን ይነግሩናል? የት ጋር ማሻሻል አለብን?’ የሚለውን የምንለይበት ነው” ብለዋል።
ኢትዮጵያ ካስቀመጠቻቸው ስትራቴጂካዊ ግቦች አንጻር በተለይ በእናቶች ጤና ዙሪያ ያስመዘገበችው ውጤት አስደናቂ መሆኑን ሚኒስትሯ አብራርተዋል። በቅርቡ ይፋ በሆነው የኢትዮጵያ የጤና እና ስነ-ህዝብ ጥናት (EDHS) መረጃ መሰረት፣ የሀገሪቱ የእናቶች ሞት ምጣኔ በከፍተኛ ደረጃ ዝቅ ብሎ 141 (በየ100,000 በህይወት ከሚወልዱ ህፃናት ውስጥ) መድረሱን ገልጸዋል። ይህ ፈጣን መሻሻል ኢትዮጵያን በአህጉሪቱ ካሉ ምርጥ ተሞክሮ ካላቸው ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ አድርጓታል።
ዶክተር መቅደስ ይህ ስኬት ዝም ብሎ የመጣ ቁጥር እንዳልሆነ ያስረዳሉ፡፡የባለሙያዎች ቁርጠኝነት፡ የጤና ባለሙያዎችን የማብቃትና የማዘጋጀት ስራ በስፋት መከናወኑ፣ ማህበረሰቡ ለጤና መረጃና ለተቋማት ያለው አመኔታ ማደጉ እና የቅድመ-ወሊድ ክትትልና በጤና ተቋማት የመውለድ ባህል መዳበሩ እና ህፃናት አምስት አመት ሳይሞላቸው የሚሞቱበትን ምጣኔ በአለም አቀፍ ደረጃ በሚደነቅ መልኩ መቀነስ መቻሉ ከዋና ዋና ምክንያቶች ውስጥ ተጠቃሽ መሆናቸውን ያብራራሉ፡፡
የ2030 ግቦችን ለማሳካት ጥቂት አመታት ብቻ መቅረታቸውን ያመለከቱት ዶክተር መቅደስ፣ ከዚህ በኋላ በተለመደው ፍጥነት ሳይሆን ፍጥነትን በከፍተኛ ደረጃ ጨምሮ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል። “ኢንቨስትመንቶቻችን የተበታተኑ ሳይሆኑ የጋራ፣ የሚሻገሩና የሚዘልቁ መሆን አለባቸው። ወደኋላ ያስቀሩንን ነጥቦች ለይተን ከፍተኛ ሀብት እንመድባለን” ብለዋል።
ኢትዮጵያ አዲሱን የ2019 የበጀት አመት ልትጀምር ባለችበት እና የ3 አመት የጤናው ዘርፍ የልማትና ኢንቨስትመንት እቅዷን ይፋ በምታደርግበት ወቅት ላይ በመሆኗ፣ ይህ ጉባኤ በወቅቱ የተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመዋል። ባለፈው ሳምንት ከ10,000 በላይ የጤና ባለሙያዎች ከተዋረድ ወረዳ ጀምሮ እስከ ክልል የጋራ ስልጠና ማድረጋቸውንም አስታውሰዋል።አዲስ አበባ የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከል ማዕከል (Africa CDC) መቀመጫ መሆኗን የጠቀሱት ሚኒስትሯ፣ የጤና ስራ ድንበር እንደሌለው አፅንዖት ሰጥተዋል።“ባክቴሪያና ቫይረሶች ድንበር የላቸውም (borderless)። ስለዚህ በክሮስ-ቦርደር (cross-border) ክትባቶችን በጋራ እንከተባለን፤ ወረርሽኞች ሲከሰቱም የቅድመ-ቅኝት ምርመራዎችን በጋራ እናደርጋለን።”
ለዚህም ማሳያ አድርገው ያነሱት፣ ኢትዮጵያ በቅርቡ የተከሰተውን የማርበርግ (Marburg) ወረርሽኝ ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከከተማው የራቀ ቦታ ቢሆንም ቶሎ ‘ኮንቴን’ በማድረግ (በመግታት) ለአህጉሪቱና ለአለም ስጋት ሳይሆን መቆጣጠር መቻሏንና ይህም ትልቅ የልምድ ማጋሪያ መሆኑን ነው።
በአሁኑ ወቅት በዲሞክራቲክ ኮንጎ እና በኡጋንዳ የተከሰተውን የኢቦላ (Ebola) ወረርሽኝ ተከትሎም፣ የድንበር ቁጥጥርና የበሽታ መከላከያ ስራዎች በከፍተኛ ‘አለርት’ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል። በሀገሪቱ በሚገኘው አለም አቀፍ የመጀመሪያ ደረጃ ጤና አጠባበቅ ውስጥ ከ10 በላይ ሀገራት ሚኒስትሮችና ከ400 በላይ አህጉራዊ ዜጎች መጥተው ስፔሻላይዝ እያደረጉና ፖሊሲ እየቀረጹ መሆኑን በመጥቀስ፣ ኢትዮጵያ በተግባር ሰርታ ለሌሎች ምሳሌ መሆን መጀመሯን አብስረዋል።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ በበኩላቸው፣ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ለመጡ ፖሊሲ አውጪዎችና ተመራማሪዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ካስተላለፉ በኋላ፣ የተቋማቸውን ታሪካዊ ጉዞና የአህጉሪቱን የመረጃ ፍላጎት ዳስሰዋል። የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከ100 ዓመታት በላይ ልምድ ያለው፣ የአፍሪካ ጥንታዊ የህዝብ ጤና ተቋም መሆኑን የገለጹት ዶክተር መሳይ፣ በአሁኑ ወቅት ተቋሙ የመረጃ አመንጪ፣ የትንታኔ፣ የህዝብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎች አስተዳደርና የጤና ደህንነት ጣልቃ ገብነት መሪ ማዕከል መሆኑን አብራርተዋል። የላቁ የላቦራቶሪ ስርአቶችና የክትትል አቅሞች እንደ ማርበርግ እና ኤምፖክስ (Mpox) ያሉ አደገኛ በሽታ አምጪ ተህዋስያንን በፍጥነት ለመለየት አስችለዋል።
ዳይሬክተሩ በአፍሪካ የጤና መዋቅር ውስጥ መዋቅራዊ ለውጥ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡“ለብዙ አመታት የጤና መረጃ ስርአቶች የተበታተኑ ወይም በውጭ ቅድሚያ በሚሰጣቸው ጉዳዮች የሚመሩ ነበሩ። ዛሬ ግን የአፍሪካ ሀገራት ባለቤትነታቸውን እያስመለሱ ነው፤ መረጃዎቻቸውን ለፖሊሲ ግብአትነት ለመጠቀምና በማስረጃ ላይ የተመሰረተ የፖሊሲ ውሳኔ አሰጣጥን ለመቅረጽ ስልቶቻቸውን እያስተካከሉ ነው” ብለዋል፡፡
ይህንን መደበኛ የጤና መረጃ ስርአት ለማጠናከር የ’ካውንትዳውን 2030′ ህብረት ትልቅ ሚና እንዳለው ጠቅሰው፣ በተለይም እንደ ‘ዳታ ስዊት’ (Data Suit) ያሉ መድረኮች መረጃን ከDHIS2 ስርአት አውጥቶ ለመተንተንና በዕይታ ለማስደገፍ የቴክኒክ እንቅፋቶችን እንደቀነሱ አስረድተዋል።
ኢንስቲትዩቱ ጥራት ያለው መረጃ በማመንጨትና እንደ ማርበርግ እና ኤምፖክስ ያሉ አደገኛ በሽታዎችን በፍጥነት በመለየት ረገድ የዳበረ አቅም እንዳለው ገልጸዋል። አፍሪካውያን በውጭ ድጋፍ ላይ ያላቸውን ጥገኝነት በመቀነስ ወደ ሀገር-በቀል የጤና መረጃ ባለቤትነት መሸጋገር እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
በተጨማሪም ዶክተር መሳይ በሳምንቱ ውስጥ የሚከናወኑት የቴክኒክ ስራዎች አራት ዋና ዋና ዓላማዎችን እንደሚከተሉ ገልጸዋል። እነዚህም በመረጃ ትንተና ላይ የቴክኒክ ክህሎትን ማሳደግ፣ ጥራት ያላቸው የትንታኔ ሪፖርቶችን ማውጣት፣ እኩልነት የሌላቸውን ቦታዎች ለመለየት በሀገራት መካከል ያለውን ትብብር ማጠናከር እና መረጃዎች ለፖሊሲ ግብአትነት ወደ ተግባር መተርጎማቸውን ማረጋገጥ መሆናቸውን በዝርዝር አብራርተዋል።
የካውንት ዳውን 2030 ዳይሬክተር ዶክተር ቼኪህ ፋይ ባደረጉት ስሜት ቀስቃሽ ንግግር፣ አዲስ አበባ የአፍሪካውያን በሙሉ ቤት መሆኗንና እዚህ በመገኘታቸው የሚሰማቸውን ኩራት ገልጸዋል። ጉባኤውን በከፍተኛ ደረጃ ላስተናገደው የኢትዮጵያ የሕዝብ ጤና ኢንስቲትዩትና ቪዛዎችን ጨምሮ መላውን የዝግጅት ስራ ላሳለጡ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
ዶክተር ቼኪህ በጉባኤው ላይ የታደሙትን 36ቱን ሀገራት ስም በየተራ በመጥራት በአዳራሹ ውስጥ የነበረውን አህጉራዊ አንድነትና ብዝሃነት አድምቀዋል። ከምዕራብ አፍሪካ (ቤኒን፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ጋና፣ ናይጄሪያ፣ ሴኔጋል… ወዘተ)፣ ከመካከለኛው አፍሪካ (ካሜሩን፣ ቻድ፣ ዲአርሲ)፣ ከምስራቅ አፍሪካ (ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ኡጋንዳ፣ ሶማሊያ…) እንዲሁም ከደቡብ አፍሪካ (አንጎላ፣ ማላዊ፣ ዛምቢያ፣ ዚምባብዌ…) የመጡ ልዑካንን አስተዋውቀዋል። እንደ ሞሪታኒያና ቦትስዋና ያሉ በጉዞ መስተጓጎል በአካል ያልተገኙ ሀገራትም በመስመር ላይ በቀጥታ እየተከታተሉ መሆኑን ጠቅሰዋል።
“ጉባኤውን ዘንድሮ ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው? ይህ ስብሰባ በአንድ አዳራሽ ውስጥ ቴክኒካዊ ትንታኔዎችን ብቻ ሳይሆን የጤና ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎችን፣ የህዝብ ጤና መሪዎችን፣ ዩኒቨርሲቲዎችንና የልማት አጋሮችን በአንድ ላይ ማቀፉ ነው” ብለዋል ዶክተር ቼኪህ። “ሁላችንም የተሰበሰብንበት አንድ ትልቅ አላማ አለ፤ እሱም፦ የተሻለ መረጃ ወደተሻለ ውሳኔ እና ወደተሻለ ውጤት መምራቱን ማረጋገጥ ነው ብለዋል፡፡
ንቅናቄው በ2005 “ካውንትዳውን 2015” ተብሎ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት 20 ዓመታት ዋና ደጋፊ ለሆነው የጌትስ ፋውንዴሽን (Gates Foundation)፣ እንዲሁም ለዓለም ጤና ድርጅት (WHO)፣ ለዩኒሴፍ (UNICEF) እና ለዓለም ባንክ (GFF) ምስጋና አቅርበዋል። ላለፉት 25 ዓመታት ከንቅናቄው በስተጀርባ ላለው ለአቶ ክሪስ ቦማ (Chris Boma) ልዩ እውቅና ሰጥተዋል።
ዳይሬክተሩ እንደገለጹት፣ አሁን ወደ ዘላቂ ልማት ግቦች (SDGs) ማብቂያ መስመር እየተቃረብን ባለበት ወቅት፣ ትኩረቱ መሆን ያለበት ዓለም አቀፋዊ እይታ ሳይሆን በእያንዳንዱ ሀገር ውስጥ ያሉ ተጨባጭ ችግሮችን መረዳት ነው። “ይህ የሥራ ስብሰባ ነው፣ ተግባራዊ ስብሰባ ነው፣ እና በሀገር ላይ ያተኮረ ስብሰባ ነው” በማለት ተሳታፊዎች በግልፅነት፣ በአዎንታዊ መንፈስና በሀገር ባለቤትነት በተዘጋጁ ውጤቶች ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ በማሳሰብ ንግግራቸውን አጠቃለዋል።
ይህ በአዲስ አበባ የተካሄደው የአመቱ ታላቅ አህጉራዊ ስብሰባ፣ አፍሪካ በጤናው ዘርፍ የሌሎችን እርዳታና መመሪያ ብቻ ጠባቂ ሳትሆን፣ የራሷን ሳይንሳዊ መረጃ በራሷ ባለሙያዎች በመተንተን የፖሊሲ ውሳኔዎችን መወሰን የምትችልበት አቅም ላይ መድረሷን ያሳየ ነው። ኢትዮጵያ በእናቶችና ህፃናት ጤና ላይ ያሳየችው አስደናቂ ዝቅታና የወረርሽኝ መከላከል ብቃት ለአህጉሪቱ ትልቅ ተሞክሮ ሲሆን፣ የ36ቱ ሀገራት የጋራ ቁርጠኝነትም እስከ 2030 ድረስ የተሻለ የጤና ስርአት ያላትና እኩልነት የሰፈነባት አፍሪካን ለመፍጠር የተጣለውን ተስፋ ይበልጥ የሚያለመልም ነው ሲሉም ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።
See less






