የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ማስተባበሪያ ማዕከል በዛሬው ዕለት በብሔራዊ ስትራቴጂክ ዕቅዱ ላይ ከክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶች፣ ከአለም አቀፍ ተቋማት፣ ከአጋር አካላት፣ ከክልል ጤና ቢሮዎች እና ከተለያዩ መንግስታዊ ተቋማት እንዲሁም ጥሪ ከተደረገላቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር ስብሰባ አካሄደ፡፡
ዶ/ር መሳይ ኃይሉ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ስብሰባውን በንግግር በከፈቱበት ወቅት እንደገለጹት ሀገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰቱ የሚችሉ የሕብረተሰብ ጤና ስጋቶችን በተገቢው ሁኔታ ምላሽ ለመስጠት ይቻል ዘንድ የተጠናከረ የዝግጁነት ምላሽ ስርዓት እንዲኖራት ማድረግ ወቅታዊና ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን በአጽንኦት አስረድተዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም የኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ማዕከል ብሔራዊ ስትራቴጂክ ዕቅድ መተግበር የሀገሪቱን የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች የአደጋ ጊዜ ምላሽ አቅምን ለማሻሻል፤ የተቋማትን ቅንጅት ለማጠናከር እና የሕብረተሰቡን ጤና ደህንነት ለማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው አስገንዝበዋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መልካሙ አብቴ በበኩላቸው የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን በብቃት ለመቆጣጠር እና ውጤታማ ምላሽ ለመስጠት በሁሉም ደረጃዎች ያለ ትብብርና ቅንጅት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ስትራቴጂክ ዕቅዱ በብሔራዊ እና በክልል ደረጃ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ ምላሽ የሚሰጡ ተቋማትን በማጠናከሩ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚደርግ አብራርተዋል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታም በኢትዮጵያ የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ እና በእንግሊዝ መንግስት የጤና ደህንነት ቢሮ ኃላፊ በስብሰባው ላይ ባደረጉት ንግግር ተቋማቱ ከዚህ ቀደም ሲያደርጉት እንደነበረው ሁሉ አሁንም ለኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ሰርቪላንሰ ዳይሬክቶሬት የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ማስተባበሪያ ማእከል ኃላፊ ወ/ት ኤቢሴ ኦቦሴ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ማስተባበርያ የዳሰሳ ወጤትን በማቅረብ፤ በቀጣይ የስትራቴጅክ እቅድ አፈጻጸምን የሚከታተል የቴክኒካል ቡድን በፌደራልና በክልል ደረጃ አስፈላጊነቱን በማስገንዘብ በቀጣይም ሁሉም በዕቅዳቸዉ ውስጥ በማካተት የታለመዉን የልሕቀት ማዕከል ዕውን በማድረግ የበኩላቸዉን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
See less






