የሲዳማ ክልል ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኩፍኝ ላቦራቶሪ ምርመራ በይፋ ተጀመረ።
የሲዳማ ክልል ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት
ግንቦት 15/ 2018ዓ.ም
በሲዳማ ክልል ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኩፍኝ ላቦራቶሪ ምርመራ በይፋ መጀመሩ ተገልጿል ።
ይህም በክልሉ እና በአጎራባች ክልሎች ለሚከሰቱ ወረርሽኞች ፈጣንና ተደራሽ የሆነ የላቦራቶሪ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ጉልህ እመርታ መሆኑ ተጠቁሟል።
ኢንስቲትዩቱ በተለያዩ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎችና ወረርሽኞች ላይ ውጤታማ ምላሽ ለመስጠት የላቦራቶሪ አቅሙን በዘመናዊ መሳሪያዎችና በሰው ኃይል እያጠናከረ መሆኑ ተገልጿል።
ከኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በትብብር ለባለሙያዎች የተሰጠውን ስልጠና ተከትሎ የኩፍኝ ተጠርጣሪ ናሙናዎች በተቋሙ ውስጥ መመርመር መጀመሩ ተገልጿል።
በስልጠናው ላይ የተገኙት የሲዳማ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የላቦራቶሪ ዳይሬክተር አቶ አዳቶ አዴላ እንደገለጹት፣ ከስልጠናው በኋላ የተሰበሰቡ ሁሉም የኩፍኝ ናሙናዎች በተቋሙ ውስጥ ተመርመረው ውጤታቸው መሰጠቱን ገልጸዋል።
አቶ አዳቶ አክለውም፣ ከዚህ ቀደም ወደ አዲስ አበባ በመላክ የሚከናወነው የኩፍኝ ምርመራ አሁን በኢንስቲትዩቱ ውስጥ ሙሉ በሙሉ መከናወን መጀመሩን ጠቅሰው፣ ይህም የምርመራ ጊዜን በማሳጠር ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ትልቅ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው ተናግረዋል ።
በተጨማሪም የህብረተሰብ ጤና አደጋዎችን በፍጥነት የመለየት፣ የመከላከል እና ውጤታማ ምላሽ የመስጠት አቅምን ለማሳደግ የላቦራቶሪ አገልግሎቶች በአለም አቀፍ ጥራት ደረጃ መሰጠታቸው አስፈላጊ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተው አብራርተዋል ።
ጠንካራ የጤና ስርዓት ለመገንባት ዘመናዊና ተደራጅተው የሚሰሩ ላቦራቶሪዎች የጤና ዘርፉ “የጀርባ አጥንት” መሆናቸውም ተጠቅሷል።
የኩፍኝ ምርመራው በክልሉ ውስጥ መጀመሩ ታካሚዎች ፈጣን አገልግሎት እንዲያገኙ፣ የናሙና መጓጓዣ ወጪና ጊዜ እንዲቀንስ እንዲሁም ለወረርሽኝ ቁጥጥር ስራዎች የተሻለ የመረጃ ፍሰት እንዲኖር አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተጠቁሟል።
የሲዳማ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት
ግንቦት 15/2018 ዓ/ም
ሀዋሳ
ለተጨማሪ መረጃዎች የሲዳማ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት:
ነፃ የስልክ መስመር፡ 7794
Web site: sphi.gov.et/emergency
See less







