የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የ100ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩውን ሊያከብር ነው፡፡
—————————
በዛሬው ዕለት የኢትዮጵያ የሕብተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳየሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ እና ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ፣ ዶ/ር ሳሮ አብደላ እና ዶ/ር መልካሙ አብቴ በጋራ በመሆን ለኢንስቲትዩቱ ሰራተኞች እና ለሚዲያ አካላት ኢንስቲትዩቱ የተመሰረተበትን መቶኛ ዓመት የአልማዝ እዮቤልዩ በዓል ከመጪው ሐምሌ 9 እስከ 11/2018 ዓ.ም በደማቅ ሁኔታ በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚያከብር አስታውቀዋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኢንስቲትዩቱ ላለፉት አንድ መቶ ዓመታት በሀገር አቀፍ ደረጃ በምዕተ አመቱ ጉዞው የሕብረተሰቡ ጤና ይጠበቅ ዘንድ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን በመከላከልና በመቆጣጠር፣ ብሔራዊ የላቦራቶሪ አቅምን በመገንባት፣ የተለያዩ ምርምርና ጥናቶችን በማካሄድ፣ የጤና መረጃዎችን በአንድ ቋት በማሰባሰብ ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ፤ የአንድ ጤና ስርአትን በማጠናከር፣ አለማቀፍ የጤና ደንቦችን በማስተግበር ረገድ በርካታና ትላልቅ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡
ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የመቶ አመቱ ክብረ በዓልና የ5ኛው የሳንይንስ ኮንግረስ ዝግጅት ኮሚቴ ሰብሳቢ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ ከምስረታው ጀምሮ ያለፈባቸውን የአወቃቀር እና የስያሜ እንዲሁም የአገልግሎት መጨመር እና መቀነስ ሁኔታዎችን አሁን እስካለበት ድረስ ያለውን ሂደት በጽሁፍ ያቀረቡ ሲሆን ከዚሁ በመቀጠልም ክብረ በዓሉ የተለያዩ ዝግጅቶችን የሚያካትት ሲሆን አዲሱ የኢንስቲትዩቱ ሪብራንዲንግም እንደሚተዋወቅ፣ ኢንስቲትዩቱን ከምስረታው ጀምሮ እስካሁን ያለውን ጉዞ የሚያሳይ መጽሀፍም በዕለቱ እንደሚመረቅ እና ለአንባቢያን እንደሚበቃ፣ 5ኛው የሳይንስ ኮንግረስ እንደሚካሄድ እና አውደ እርዕዮችም እንደሚኖሩ ገልጸዋል፡፡
የላቦራቶሪ አመሰራረት በኢትዮጵያ ምን እንደሚመስልና ብሎም እንዴት አሁን ኢንስቲትዩቱ የተመሰረተበት ቦታ ስራ እንደጀመረ እና አሁን ካለው የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር ያለውን ስራ ሁሉ ከመጀመሪያው ጀምሮ በማያያዝ ያቆየው የላቦራቶሪ አገልግሎት መሆኑን ያስረዱት ደገሞ የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሳሮ አብደላ ናቸው፡፡ እንደ ዶ/ር ሳሮ ገለጻ በኢንስቲትዩቱ ለላቦራቶሪ አገልግሎት መሰረተ ድንጋይ የተጣለው እ.ኤ.አ 1922 ሲሆን አገልግሎት የጀመረው ደግሞ እ.ኤ.አ 1924 ነው፡፡
See less






