ለወረርሽኝ ምላሽ ዝግጁ የሆኑ ተቋማትን ማዘጋጀት የጤናውን ዘርፍ ለማጠናከር ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ፡፡
በድንገት ለሚከሰቱ ልዩ ልዩ ወርረሽኞች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ይቻል ዘንድ ለወረረሽኝ ዝግጁ የሆነ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና ተቋማትን ዝግጁ ማድረግ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ተገለጸ፡፡
ክቡር ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ላለፉት ሁለት አመታት በአዲስ አበባ፤ በሲዳማ እና በደቡብ ኢትዮጵያ በ197 የጤና ተቋማት ላይ ሲተገበር የቆየውን “ለወርረሽኝ ዝግጁ የሆነ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና አሀድ ፕሮግራም” ላይ በመገኘት ባደረጉት ንግግር የማይበገር የጤና ስርዓት መገንባት ከሚቻልባቸው መንገዶች አንዱ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና አሀድ እና ወርረሽኞችን ለመከላከል የሚሰሩ ልዩ ልዩ መሰረታዊ ስራዎች እንደሆኑ ጠቅሰው እነዚህ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አያይዘውም ለወርረሽኝ ዝግጁ የሆኑ የጤና ተቋማትን ቀድሞ ማዘጋጀት መቻሉ ያለውን ጠቀሜታን በተመለከተ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው በቅርቡ በሀገራችን በጂንካ ላይ ተከስቶ የነበረውን የማርበርግ ወረሽኝ በሽታ በዘጠና ቀናት ውስጥ በተሳካ ሁኔታ መቆጣጠር መቻሉ እንደሆነ አውስተው ይህን መሰል የሚሰሩ ስራዎች ቀጣይነትና ዘላቂነት ሊኖራቸው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በተለይ ተቋማት ግንባታ፤ ባለሙያዎችን የማብቃትና ደህንነታቸውን የመጠበቅ ብሎም በፍጥነት ቶሎ ወርረሽኞችን የማወቅ ሪፖርት የማድረግ እና ምላሽ የመስጠት የመሳሰሉት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል፡፡
ዶ/ር መሳይ ሀይሉ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው የተጠናከረ ለወርረሽኝ ዝግጁ የሆነ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና አሀድ ፕሮግራም መኖር ለጤና ደህንነት ወሳኝ መሆኑን አውስተው ለወርረሽኝ ዝግጁነትን ከመጀመሪያ ደረጃ የጤና ፕሮግራሞች ውስጥ በማካተት ጠንካራና የማይበገር ስርዓትን ለመገንባት እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም ከቅርብ ጊዚያት ተሞክሮዎች መረዳት እንደሚቻለው ወርረሽኞች ሲከሰቱ ህብረተሰቡ የሚገለገልባቸው የዕለት ተዕለት መሰረታዊ የሆኑ የጤና ፕሮግራሞች ሳይስተጓጎሉ እና ሳይቋረጡ መስጠት መቻሉ ከተመዘገቡት ውጤታማ ስራዎች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን አውስተዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አሁን በሶስት ክልሎች የተመዘገበው ይህ ውጤታማ ፕሮግራም በመላው ሀገሪቷ እንዲስፋፋ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር መልካሙ አብቴ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር በሀገሪቱ የሚከሰቱ ወርረሽኞችን ለመከላከል ይቻል ዘንድ ቀጣይነት ባለው መልኩ በጤና ተቋማት ላይ የሚሰሩ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አስፈላጊ የሆኑ ስራዎች ሁሉ እንደሚከናወኑ አስረድተዋል፡፡
አቶ ግርማ ደሴ የሪዞልቭ ቱ ሴቭ ላይቭ ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው ላለፉት ሁለት ዓመታት ይህ ፕሮግራም ውጤታማ እንዲሆን የተሳተፉትን መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላትንና ባለሙያቸውን በሙሉ አመስግነዋል፡፡
See less







