የሲዳማ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ክብርት ፋንታዬ ከበደ የሚመሩት የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎችና አመራሮች ቡድን፣ የ2018 በጀት ዓመት የጤና ዘርፉን አፈጻጸም ለመገምገም የመስክ ጉብኝት ጀምረዋል።
የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ሐምሌ 16/2018 ዓ.ም
የሲዳማ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ክብርት ፋንታዬ ከበደ የሚመሩት የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎችና አመራሮች ቡድን፣ በ2018 በጀት ዓመት በጤና ዘርፉ የተከናወኑ ሥራዎችንና የአፈጻጸም ውጤቶችን በተጨባጭ ለመገምገም የመስክ ጉብኝት ጀምረዋል።
የጉብኝቱ መነሻ ደቡባዊ ሲዳማ ዞን በአለታ ወንዶ ወረዳ የሚገኘው የቤለስቶ ጤና ጣቢያ ሲሆን፣ በጤና ጣቢያው ውስጥ የተደራጁ የህክምና አገልግሎት ክፍሎችን፣ የመድኃኒት አቅርቦትና አስተዳደርን፣ የጤና ሴክተር ሪፎርም ትግበራን እንዲሁም ለተገልጋዮች ምቹ፣ ጽዱ፣ ውብና ማራኪ የአገልግሎት አካባቢ ለመፍጠር የተከናወኑ ሥራዎችን በቦታው በመገኘት ተመልክተዋል።
በተጨማሪም በተቋሙ እየተተገበረ ባለው የእናቶችና የሕፃናት ጤና ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ፣ በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን (CBHI) አፈጻጸም፣ በተመዘገቡ ውጤቶችና በቀጣይ የማሻሻያ እቅዶች ዙሪያ ለቋሚ ኮሚቴዎቹ ዝርዝር ገለጻ ቀርቧል።
በገለጻውም የእናቶችና የሕፃናት ጤናን ለማሻሻል የተወሰዱ እርምጃዎች፣ የአገልግሎት ተደራሽነትና ጥራት ለማሳደግ የተከናወኑ ተግባራት፣ እንዲሁም የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አገልግሎትን ለማስፋፋት የተሰሩ ሥራዎች በስፋት ተብራርተዋል።
ቋሚ ኮሚቴዎቹና አመራሮቹ በጉብኝቱ ወቅት የተመለከቷቸው የለውጥና የሪፎርም ሥራዎች፣ በአገልግሎት ጥራት ማሻሻያ የተመዘገቡ ውጤቶች አበረታች ጅምር መሆናቸውን ገልጸው፣ በተቋሙ የተፈጠሩ መልካም ተሞክሮዎች በሌሎች የጤና ተቋማትም ተስፋፍተው እንዲተገበሩ አስፈላጊ መሆኑን አሳስበዋል።
የመስክ ጉብኝቱ ለቀጣዮቹ ሁለት ቀናት የሚቀጥል ሲሆን፣ በሲዳማ ክልል በሚገኙ የተለያዩ ዞኖች ሥር ያሉ የጤና ተቋማትን በመጎብኘት የ2018 በጀት ዓመት የጤና ዘርፉ አፈጻጸም በተጨባጭ እንደሚገመገም ተገልጿል።
የሲዳማ ክልል መንግሥት ጤና ቢሮ
ሐምሌ 16/2018 ዓ.ም
ለተጨማሪ የመረጃ አማራጮች
![]()
![]()
![]()
ይመልከቱ
Website: https://www.shb.gov.et
Facebook:




Telegram : https://t.me/SidamaRHB
Twitter: https://x.com/sidama_health_bureau
WhatsApp:
YouTube:
Tik Tok:
See less






