የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቱ አለምአቀፋዊ ደረጃ ላይ የሚገኝ ታላቅ የምርምር ተቋም መሆኑ ተገለጠ።
በዛሬው ዕለት በከፍተኛ ድምቀት መከበር በጀመረው የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት 100ኛ ዓመት የምስረታ ክብረ በዓል ላይ ክብርት ዶ/ር መቅደስ ዳባ
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የጤና ሚኒስትር ባደረጉት ንግግር ላይ እንዳስታወቁት ላለፉት 100 ዓመታት ተቋሙ የሳይንሳዊ ብቃት፣ የፈጠራ ሥራ እና የሀገር አገልግሎት ጠንካራ ምሰሶ ሆኖ በመቆየቱ በበሽታ ቅኝትና ክትትል፣ በላቦራቶሪ አገልግሎቶች፣ በምርምር፣ በህብረተሰብ ጤና አደጋ ዝግጁነትና ምላሽ እንዲሁም በሥነ-ምግብ እና በህዝብ ጤና መረጃ ሥርዓቶች አማካኝነት የኢትዮጵያን ህዝብ ጤናና ደህንነት ለመጠበቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አስረድተዋል።
ክብርት የጤና ሚኒስትሯ አያይዘውም ይህ ክብረ በዓል ራዕይ ያላቸውን መሪዎች፣ ቁርጠኛ ሳይንቲስቶችን፣ የላቦራቶሪ ባለሙያዎችን፣ ተመራማሪዎችን፣ የህዝብ ጤና ባለሙያዎችን እና የድጋፍ ሰጪ ሰራተኞችን የምናመሰግንበት እና የምናከብርበት ልዩ አጋጣሚ ከመሆኑም በላይ የእነሱ ትጋትና መልካም ስራ ቱሩ ፋቶች በአሁኑ ወቅት እንስቲትዮቱን በአፍሪካ ከሚገኙ ቀዳሚ የህዝብ ጤና ተቋማት አንዱ አድርጎታል ብለዋል።
ዶ/ር መቅደስ አያይዘውም በአሁኑ ወቅት የህዝብ ጤና ተግዳሮቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተወሳሰቡ መምጣታቸውን ገልፀው ለእነዚህ ተግዳሮቶች ማለትም አዳዲስና ተመላላሽ ተላላፊ በሽታዎች፣ የፀረ-ተዋህሲያን መድሀኒቶችን መቋቋም፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የሥነ-ምግብ ችግሮች እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ለመመከት ይቻል ዘንድ ጠንካራ ተቋማትን መገንባት፣ ጠንካራ ሳይንሳዊ ሥራን ማከናወን እና የተጠናከረ ትብብር ማዕቀፍን ማጠናከር ትኩረት ሊሰጥበት የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ በአፅንኦት ተናግረዋል።
በመጨረሻም ተቋሙ ለሁሉም ዜጎች ፍትሃዊና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለማረጋገጥ እና የሁሉንም ህዝብ የጤና ሽፋን ለማሳካት በምርምር፣ በላቦራቶሪ አቅም፣ በበሽታ ቅኝትና ክትትል፣ በዲጂታል ጤና፣ በሰው ኃይል ልማት እና በጤና አደጋ ዝግጁነት ላይ በመዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ የህዝብ ጤና ሥርዓቱን ለማጠናከር ቁርጠኛ በመሆኑ አመስግነው የሚኒስቴር መ/ቤቱ ያልተቆጠበ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
See less






