Sidama Hawassa
+251-462-12-6495
dagoomuf@sidaamaphi.org

የጤና ሚኒስቴር አመራሮችና ባለሙያዎች ባለፉት አራት ቀናት በሲዳማ ክልል ሲያደርጉት የነበረውን የተቀናጀ ድጋፋዊ ክትትል አጠናቀው ግብረ መልስ ሰጡ !

የጤና ሚኒስቴር የተቀናጀ ድጋፋዊ ክትትል (ISS) ቡድኑ በሁለት ቡድኖች ተከፋፍለው ባለፉት አራት ቀናት ተዘዋውረው የሥራ እንቅስቃሴያቸውን ከተከመለከቷቸው ጤና ተቋማትና መዋቅሮች መካከል :-

የክልሉ ድንገተኛ ክስተቶች መከታተያ ስርዓት (EOC )የክልሉ ጠቅላላ ላቦራቶሪ ፣ ሁለት (2 ) ዞኖችና ሀዋሳ ከተማ (1) ፣ አራት (4) ሆስፒታሎች ፣ አምስት (5) ወረዳዎች ፣ ስምንት (😎 ጤና ጣቢያዎች ፣ ሰባት (7) ጤና ኬላዎች እና ሰላሣ ሁለት (32) አባወራ/እማወራ ደረጃ በወባ መከላከልና ቁጥጥር ዙሪያ የተሰሩ ስራዎችን ቅኝት አድርገው የክልሉ የብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ ክቡር አቶ አብርሃም ማርሻሎ በያዙት መድረክ የጤና ቢሮ አመራሮች በተገኙበት ግብረ መልስ ሰጥተዋል።

ቡድኑን በመወከል ግብረ መልስ ያቀረቡት የኢፌዲሪ የመድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር አብዱልቃድር ገልገሎ ነበሩ።

የድጋፋዊ ክትትሉ ቡድን ትኩረት ከሰጡባቸው ጉዳዮች መካከል ፥ በክልሉ ወባን ለመከላከል የህብረተሰብ ተሳትፎ ያለበት ደረጃ ፣ የመከላከያ ስልቶች አተገባበርና ተጠቃሚነት ፣ ጤና ተቋማት ለወባ ታካሚዎች እየሰጡ ያሉት የሕክምና አገልግሎት ጥራት ምን እንደሚመስል እና በመጀመሪያ ደረጃ የጤና ክብካቤ አሃድ ትስስር ወባን ለመከላከል የሚሠሩ ስራዎች ምን ያህል ጠንካራ እንደሆነ ታሳቢ ያደረጉ ነበሩ።

መድረኩን የመሩት የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ ክቡር አቶ አብርሃም ማርሻሎ ፥ በድጋፋዊ ክትትሉ የተለዩ ጠንካራ ጎኖች ይበልጥ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እና በቡድኑ እይታና ግምገማ መሠረት የተስተዋሉ ጉድለቶችን ደግሞ በየደረጃው የሚገኙ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ፈጥነው ማስተካከል እና የወባ በሽታ በክልሉ ችግር ወደማይሆንበት ደረጃ ማድረስ እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

ክቡር አቶ አብርሃም አክለውም ቡድኑ የክልላችንን መዋቅሮች እና ጤና ተቋማትን በአካል በመገኘት ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።

የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሰላማዊት መንገሻ በበኩላቸው ከጤና ሚኒስቴር ድጋፋዊ ክትትሉ ቡድን የክልሉ ጤና ባለሙያዎቻችን የተሻለ ግንዛቤ እንዲያገኙ ያስቻለ ድጋፍ እንደተደረገላቸው አንስተው ቡድኑን አመስግነዋል። ከድጋፋዊ ክትትሉ ቡድን ግኝት አኳያ በጥንካሬ የተለዩ ጉዳዮችን ለማስቀጠል እና በክልሉ በኩል ሊስተካከሉ የሚገቡ ጉዳዮችን ደግሞ ለማስተካከል ከፍተኛ ቁርጠኝነት በክልሉ እንዳለ ገልጸው ፥ በሌላ በኩል ደግሞ የጤና ሚኒስቴርም አንዳንድ ለጤና ተቋማት የሚያስፈልጉ የሕክምና መሣሪያዎችና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ድጋፍ እንዲያደርግልን ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ

ሕዳር 26/2017 ዓ.ም

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *